በኮሮናቫይረስ የወረርሽኝ 'ዘመን' ተስፋ የሚሰጡ 5 ነገሮች

የኮሮናቫይረስ ወርሽኝ በዓለም ሕዝብ ላይ ፈተናን በደቀነበት በዚህ ጊዜ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ እየሞቱም ነው፤ ከተሞችና አገራትም እንቅስቃሴዎችን በሙሉ አግደው ተቆልፈዋል።

ብዙዎችም ራሳቸውን ለይተው ተቀምጠዋል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በረራዎች በስፋት እየተሰረዙ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩም ሠራተኞች ከቤታቸው እየሰሩ ነው። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ጭንቅ ውስጥ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አልታጡም።

1.የአየር ብክለት መቀነስ

አገራት እንቅስቃሴዎችን ሲገቱ የአየር ብክለ በከፍተኛ መጠን መቀነሱ እየተገለፀ ነው። በቻይናም ሆነ በሰሜናዊ ጣልያን አየርን በከፍተኛ ደረጃ የሚበክለው ናይትሮጅን ዳይኦክሳይድ በጣም ቀንሷል። ይህ የሆነው የኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በመገታቱ ነው።

ኒውዮርክ የሚገኙ አጥኚዎች ለቢቢሲ እንደገለፁት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በተለይም ከመኪናዎች ሚወጣው ካርቦን ሞኖክሳይድ በ50 በመቶ ቀንሰሷል።

2.የመተላለፊያዎች ከሰዎች ጭንቅንቅ ነፃ መሆን

የባህር ላይ ጉዞዎች በመቀነሳቸውም ውሃዎች ንፁህ እየሆኑ መምጣታቸው ሲነገር በጣልያኗ ቬኒስ ከተማ የሚያቋርጠው ውሃም ይህው ለውጥ እንደታየበት ነዋሪዎች ገልፀዋል። ይህ የሆነው ለወትሮው በቱሪስቶች በሚጨናነቁት የሰሜናዊ ጣልያን ጎዳናዎች ኦና በመሆናቸው ዝቃጮች በመቀነሳቸው ነው።

የወሃው አካላት ንጹህ እየሆኑ መምጣት ውሃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አሳዎችን በግልፅ ማየት ማስቻሉም እየተገለፀ ነው።

3.የደግነት ተግባራት

ምንም እንኳ የቫይረሱ ስርጭትን እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ የጥድፊያና የድንጋጤ ግብይቶች ብዙዎችን ላላስፈላጊ ንግግርና ብሎም ድብድብ ቢጋብዝም ኮሮናቫይረስ ዓለም ላይ ደግነትን በስፋት ቀስቅሷል ማለት ይቻላል።

ሁለት የኒውዮርክ ነዋሪዎች በ72 ሰዓታት ውስጥ ብቻ አስፈላጊ የፍጆታ እቃዎችን እንዲሁም መድሃኒቶችን ለአዛውንቶችና ለሌሎች ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች በፍቃደኝነት የሚያደርሱ 1300 በጎ ፍቃደኞችን ማሰባሰብ ችለዋል።

ፌስቡክ እንዳለው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእንግሊዝ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በሚደረገው የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በፈቃደኝነት ለማገልገል ዝግጁ ሆነዋል።

ተመሳሳይም በጎ ፍቃደኞች ካናዳ ውስጥ ሌሎችን ለመርዳት የሚኣስችላቸውን ቡድን መመስረታቸው ተገልጿል።

የአውስትራሊያ ሱፐርማርኬቶች "የአዛውነቶች ሰዓት" በማለት አዛውነቶችና አካል ጉዳተኞች ያለምንም ግፊያና ግርግር የሚፈልጉትን መሸመት የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችተዋል።

በሌላ መልኩ ደግሞ ብዙ ሰዎች ገንዘብ እየለገሱ ነው፤ በተጨማሪም ራሳቸውን አግልለው ለሚገኙ ሰዎች የሞራል ድጋፍ እያደረጉና ሃሳብ እየሰጡ ነው።

የተጠቀሱት አይነት የበጎ አድራጎት ሥራዎችና ድጋፎች ኢትዮጵያ ውስጥም በስፋት እየተስተዋሉ ነው።

4.በአንድነት መቆም

በሥራና በሌሎች ኃላፊነቶች ምክንያት በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር መራራቅ የዘመኑ ኑሮ ሁነኛ መገለጫ ነው። አሁን ግን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ይህ መራራቅ አስቀርቶ ይልቁንም የዓለም ህዝብ ምንም እንኳ ርቀት ቢኖር በአንድ ላይ እንዲቆም አድርጓል።

በጣልያን በእንቅስቃሴ እገዳ ከቤት የማይወጡ የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች በየመስኮታቸው ወጥተው አንድ ላይ በመዘመርና ለጤና ባለሙያዎች የምስጋና ጭብጨባ በማድረግ በጎነትን ማወደሳቸው የዚህ አንድ ማሳያ ነው።

ብዙዎች ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ከወዳጅ ከጓደኛ ጋር ባሉበት ሆነው በስልክና በማኅበራዊ ሚዲያ ለመገናኘት እንደ እድል እየተጠቀሙበት ነው።

5.የፈጠራ ችሎታ ማበብ

ብዙዎች በቫይረሱ ከቤት መዋላቸውን ተከትሎ አጋጣሚውን የፈጠራ ችሎታቸውን ለማውጣት እየተጠቀሙበት ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አዳዲስ ልማዶችን እያመጡ መሆኑ እየታየ ነው። አንዳንዶች ማብሰልን ሌሎች ደግሞ ስዕል መሳልን አዲስ ልማድ አድርገዋል። ማንበብ ላይ ያተኮሩም እንዲሁ አሉ።