ዓለምን ያስቆጣው የህንድ አስገድዶ መድፈር ወንጀል ተጠያቂዎች በስቅላት ተቀጡ

አራቱ ወንጀለኞች

የፎቶው ባለመብት, Delhi police

ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት በህንድ አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪን አውቶቡስ ውስጥ ለስድስት ደፍረው የገደሉት በስቅላት ተቀጡ።

ከስድስቱ ደፋሪዎች አንደኛው እስር ቤት ሳለ ራሱን ያጠፋ ፤ የ17 ዓመት ወጣት የነበረው ሌላኛው ሶስት ዓመት ታስሮ እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ላይ የተፈታ በመሆኑ አሁን በስቅላት የተቀጡት አራቱ ናቸው።

ህንድ ታዳጊውን ለሶስት ዓመት በእስር እንዲቆይ ያደረገችው ለታዳጊ የሚሰጠውን ከፍተኛ ቅጣት በመፍረድ ነው።

የ23 ዓመቷ የፊዚዮቴራፒ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የተደፈረችው በመንቀሳቀስ ላይ በነበረ አውቶቡስ ውስጥ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በኋላ የሞተችውም ደፋሪዎቿ ባደረሱባት ከባድ ድብደባ ነበር።

የወጣቷ መደፈር ድፍን ህንድን አስቆጥቶ የነበረ ሲሆን መንግሥትም ፀረ አስገድዶ መድፈር ህግ እንዲያወጣ አስገድዷል።

ህንድ ጥፋተኞችን በስቅላት ስትቀጣ ከ2015 ወዲህ ይህ የመጀመሪያዋ ነው።

ጥፋተኞቹ በስቅላት እንደተቀጡ የሟች እናት " የልጄን ፎቶ አቅፌ በመጨረሻም ፍትህ ማግኘታችንን ነገርኳት" ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

አባቷም ከዚህ ወዲህ በአገሪቱ ፍትህ ስርዓት ላይ እምነት መጣል እንደሚቻል ሃሳባቸውን ገልፀዋል።

አራቱ ወንጀለኞች በስቅላት ከተቀጡበት እስር ቤት ደጃፍ በርካታ ህንዳዊያን የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የነበረ ሲሆን ልክ ስቅላቱ መፈፀሙን እስር ቤቱ ሲያስታውቅ ብዙዎች ደስታቸውን ገልፀዋል።

በስቅላት የተቀጡት አራቱ ደፋሪዎች ቅጣታቸው ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀነስላቸው ፊርማ በማሰባሰብ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።