የሴቶች ጤና፤ ሴቶችን ቆመው እንዲሸኑ የሚያስችለው ቱቦ

ኬንያዊቷ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በመጠቀማቸው ለኢንፌክሽን የሚዳረጉ ሴቶችን እፎይታ ይሰጣል ያለችውን መላ ዘይዳለች።
ኒጀሪ ሙታካ የተባለችው ይህች ኬንያዊት፤ የዘይት አሊያም የነዳጅ ማንቆርቆሪያ መሳይ ሽንት መሽኛ ቱቦዎችን ለገበያ ያቀረበች ሲሆን ቱቦው ሴቶች እንደቆሙ መሽናት እንዲያስችላቸው ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
ቱቦው ሴቶች በሕዝብ መገልገያ በሆኑ መፀዳጃ ቤቶች ተቀምጠው ከመሽናት ያድናቸዋል ተብሏል።
ኒጀሪ በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በተደጋጋሚ ከተጋለጠች በኋላ የመሽኛ ቱቦዎችን ከውጭ ማስመጣት እንደጀመረች ለቢቢሲ ተናግራለች።
ታዲያ ይህንኑ የመሽኛ ቱቦ መጠቀም ከጀመረች በኋላ ያጋጥማት የነበረው ኢንፌክሽን እንደቀነሰላት ገልፃለች።
በመሆኑም እርሷን የረዳትን መላ ለሌሎች ሴቶች መሸጥ መወሰኗንም አስረድታለች።
የህክምና ባለሙያዎችም ይህ መላ ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስ ይስማማሉ።
ዶ/ር ክሪስ ኦብዋካ "ሴቶች ለመሽናት ሲሉ ቁጭ አላሉም ማለት ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫዎች ጋር ያለ ንክኪ አይኖራቸውም ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድላቸውን ይቀንሳል። በመሆኑም ራስን ከበሽታ መከላከል ይቻላል" ብለዋል።
ይሁን እንጅ ቱቦዎቹን መጠቀም ከባህል ጋር የሚጋጭ ድርጊት ነው ሲሉ የኬንያ ወንዶች ተቃውሞ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሳይመን ባራዛ የተባለ አንድ ግለሰብ "ይህ ከባህላችን ጋር የማይሄድ ነው፤ ምክንያቱም ሴቶች ቆመው እንደማይሸኑ ነው የምናውቀው" ብሏል።
መሽኛ ቱቦው በሁለት ዶላር የሚሸጥ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ እስካሁን 400 ቱቦዎችን እንደሸጠች ኒጀሪ ተናግራለች።















