በሺዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ተማሪዎች የኢሜላቸውን ይለፍ ቃል ለማግኘት ወረፋ ይዘዋል

አዲስ የኢሜል ይለፍ ቃል ለማግኘት የተሰለፉ ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Katrina Friese

በጀርመን 38ሺህ ተማሪዎች ኢሜላቸውን ለመክፈት እንዲችሉ አዲስ የይለፍ ቃል ለማግኘት በአካል ተገኝተው ወረፋ እንዲጠብቁ መደረጉ ተሰማ።

ይህ የሆነው ዩኒቨርስቲው የሳይበር ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ነው።

በጁስቱስ ሊቤግ ዩኒቨርስቲ (ጄኤልዩ) ተማሪ የሆኑት "ሕጋዊ አሰራር" በሚል ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያቀርቡም ተጠይቀዋል።

ከሳምንት በፊት የደረሰው የሳይበር ጥቃት በአጠቃላይ የዩኒቨርስቲው ኢንተርኔትን ከስራ ውጪ አድርጎት ነበር።

ተማሪዎች ስለጥቃቱ ከተገለጸላቸው በኋላ ከጀርመን የሳይበር ደህንነት ጥናት ማዕከል ጋር በመሆን ምርመራ እየተደረገ ነው ተብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ባወጣው ማስታወቂያ ላይ " ሁሉም የዩኒቨርስቲው ሰራተኞችና ተማሪዎች በአካል በመገኘት የኢሜል ይለፍ ቃላቸውን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል" ብሏል።

ተማሪዎቹ መታወቂያ ካርዳቸውን በመያዝ ወደ ዩኒቨርስቲው የአካል ብቃት መስሪያ ስፍራ በትውልድ ቀናቸው ቅደም ተከተል መሰረት እንዲመጡ ተጠይቀዋል።

በተለጠፈው ዝርዝር መሰረት ተማሪዎቹን በሙሉ አስተናግዶ ለመጨረስ አምስት ቀናትን ይወስዳል።

ይህ በእንዲህ እያለ ዩኒቨርስቲው 1200 የፍላሽ ዲስኮች ለሰራተኞቹ ያዘጋጀ ሲሆን፤ በዚህም ሁሉም በዩኒቨርስቲው የሚገኙ ኮምፒውተሮችን ከቫይረስ እንዲጸዱ ይደረጋል ብሏል።