በግጭት አዙሪት ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች

የፎቶው ባለመብት, Diredawa University Facebook page
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ሃሙስ ምሽት ካፌ ውስጥ እራት ላይ ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ፤ እስካሁን እየተጣራ ቢሆንም አርብ ጠዋት ደግሞ የአንድ ተማሪ ከፎቅ ወድቆ ወይም ተወርውሮ መሞትን ተከትሎ ተማሪው በአጥር እየዘለለ ግቢውን ጥሎ መውጣቱን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ህብረት የሴቶች ፕሬዝዳንት የአብስራ አስፋው ትናገራለች።
ከእሷና አንድ ስሙ እንዲገለፅ ካለፈለገ ሌላ ተማሪ እንደሰማነው ተማሪዎች በአጥር እየዘለሉ ለመውጣት የተገደዱት የዩኒቨርሲቲው በር ተማሪዎች እንዳይወጡ ዝግ በመደረጉ ነው።
ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ የተቋረጠው ትምህርትም ዛሬ ሊጀመር ታስቦ የነበረ ቢሆንም አብዛኛው ተማሪ በአጥር ዘሎ በመሄዱ ግቢው ውስጥ በቀረው ጥቂት ተማሪ ይህን ማድረግ እንዳልተቻለ ተማሪዎቹ ገልፀውልናል።
ከተማሪዎቹ መረዳት እንደቻልነው ምንም እንኳ ከሃሙስ ምሽቱ ወዲህ ጉልህ የሚባል አለመረጋጋት በዩኒቨርሲቲው ባይኖርም ተማሪዎች ግን ከፍተኛ ስጋት ስላደረባቸው ግቢውን እየለቀቁ ነው።
ሴት ተማሪዎች ተደፈሩ የሚል መረጃ እየወጣ ስለመሆኑ ጥያቄ ያቀረብንላት የአብስራ በተማሪው ዘንድ ሴቶች ተደፍረዋል የሚል ወሬ እየተወራ ቢሆንም ለተማሪዎች ህብረት ለስርዓተ ፆታ ቢሮም የቀረበ ሪፖርት እንደሌለ ትገልፃለች።
"ዶርም ለዶርም እየሄድን ጠይቀናል ፤ሆስፒታልም ሄድን ለማጣራት ሞክረናል"የምትለው የአብስራ በሃሙስ እለቱ የካፌ ግርግር ወገባቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሴት ተማሪዎች ሆስፒታል ሄደው እንዳገኙ ታስረዳለች።
ዩኒቨርሲቲው እየተጠበቀ ያለው በፌደራል እና በመከላከያ አባላት እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ደግሞ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ከኦሮሚያ ክልል የሄዱ በርካታ ተማሪዎች 'ወደ መጣንበት እንመለስ" በማለት የተቃውሞ ድምፅ ማሰማታቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ገልፀውልናል።
ባለፈው ሳምንት ከፌደራልም፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል የሚመለከታቸው ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሌለባቸው፤ ይልቁንም ትምህርታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ተገልፆላቸው የነበረ ቢሆንም አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነው ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ተማሪዎች የሚናገሩት።
ተማሪዎቹ እንደሚሉት ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ አንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰባስበው ለማደር ተገደዋል። እንቅስቃሴያቸው በመገደቡም ለተለያዩ አገልግሎቶች ችግር ተጋልጠዋል።
አንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስቦ ማደር፣ በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ውስጥ መንቀሳቀስ አለመቻል በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ታይቷል።
ባለፈው ሳምንት በደምቢደሎ ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ክልል የሆነ ተማሪ በስለት ተወግቶ መሞቱን ተከትሎ ተማሪዎች ፍርሃት ውስጥ ገብተው በተመሳሳይ ነገር ውስጥ ለማለፍ ተገድደዋል።
ጥቂት በማይባሉ የኦሮሚያና አማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች በግጭት እየተገደሉ እና እየቆሰሉ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ዛሬ ነገሮች ረገቡ ትምህርት ተጀመረ ወይም ሊጀመር ነው ሲባል ግጭቶች እያገረሹ ጥቂት በማይባሉ የመማር ማስተማር ሂደት እንደተቋረጠ ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር እንዳይወጡ መከልከልም ብዙ ጥያቄዎች እያስነሳና ችግር እያስከተለ እንዳለም አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፍ ሳምንት ማብቂያ ከሚመለከታቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከደህንነት ሃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ በመከሩበት ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች የማይረጋጉ ከሆነ መንግሥት እስከ መዝጋት እርምጃ እንደሚወስድ ገልፀዋል።
ሆን ብለው ረብሻ የሚቀሰቅሱ ተማሪዎችን ህግ ፊት የማቅረብ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።
አሁንም ግን የዩኒቨርሲቲዎች ቀውስ በዘላቂነት የሚፈታው እንዴት ነው? የሚለው በቀላሉ የሚመለስ የማይመስል ጥያቄ ነው።













