የዘመናዊ ሰው መነሻ በቦትስዋና መገኘቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ቦትስዋና የሚገኘው ዛምቢዚ ወንዝ ዛሬ ላይ በጨው ግግር ቢሸፈንም ጥንት በሰፊ ሀይቅ የተሸፈነ ቦታ ነበር። ይህ አካባቢ የዘመናዊ ሰው ዝርያ መነሻ እንደሆነ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
አካባቢው ከ200,000 ዓመታት በፊት የነበሩ ሰዎች መኖሪያ ነበር ተብሎ ይታመናል። በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ለ70,000 ዓመታት ያህል በሥፍራው ኖረዋል። የአካባቢው የአየር ንብረት ሲለወጥ ግን ለም መሬት ፍለጋ መሰደዳቸውን ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
አውስትራሊያ በሚገኘው 'ጄኔቫ ኢንስቲትዮት ኦፍ ሜዲካል ሪሰርች' የተባለ ተቋም የዘረ መል ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጄነሳ ሀይስች እንደሚሉት፤ ከ200,000 ዓመታት በፊት ዘመናዊ የሰው ልጅ አፍሪካ ውስጥ ስለመኖሩ ማስረጃ አለ።
"የሰው ልጆች መነሻ አካባቢ የት ነው? የሚለውና እንዴት ወደሌሎች አካባቢዎች እንደተጓጓዙ ለዓመታት አከራካሪ ነበር" ሲሉ አስረድተዋል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፤ ጥንታዊ ሰዎች ማካጋዲካጋዲ የተባለ ሀይቅ አካባቢ ሰፍረው ነበር። በዚህ ለምለም ቦታ ለ70,000 ዓመታት ከኖሩ በኋላ ወደሌሎች አካባቢዎች ተጉዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Chris Bennett, Evolving Picture, Sydney, Australia
ተመራማሪዎቹ የሰው ልጆችን ዘረ መል ናሙና በመውሰድ እና የአየር ንብረት ለውጥን በማጥናት አፍሪካ ከ200,000 ዓመታት በፊት ምን ትመስል እንደነበር የሚያሳይ ሞዴል ሠርተዋል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ተመራማሪዎች የሰው ልጆችን ዘረ መል በማጥናት ብቻ የሰው ልጆች መነሻ ይህ አካባቢ ነበር ለማለት አይቻልም ሲሉ አዲሱ ጥናት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
የሰው ልጆች ቅሪተ አካል ላይ በተሠራ ጥናት የሰው ልጅ መነሻ ምስራቅ አፍሪካ መሆኗን የሚያሳይ መረጃ መገኘቱን እንደማስረጃ በመጠቀም የተከራከሩም አሉ።












