እስራኤል በቁፋሮ መስጂድ አገኘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስራኤል ኔጌቭ በረሀ አርኪኦሎጂስቶች 1200 ዓመት ዕድሜ ያለው መስጂድ በቁፋሮ ማግኘታቸው ተነገረ። መስጂዱ ዓለም ላይ ጥንታዊ ከሚባሉት መካከል እንደሚመደብ ተገልጿል።
ወደ ሰባተኛውና ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ዕድሜያቸውን የሚቆጥሩ ቅሪቶች የተገኙት በራሀት ቤድዌን ከተማ ነው።
የእስራኤል ቅርስ ጥበቃ እንዳለው፤ መስጂዱ ሊገኝ የቻለው በአካባቢው ለግንባታ ተብሎ ቁፋሮ በሚካሄድበት ወቅት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Israel's Antiquities Authority

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በአካባቢው በዚህ ክፍለ ዘመን የነበረ እና በመካ እና እየሩሳሌም ከተገኙት መስጂዶች ጋር በእድሜ የሚፎካከር ቅርስ ነው" ሲል የእስራኤሉ የቅርስ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ተናግሯል።
ቁፋሮውን የመሩት ባለሙያዎች በበኩላቸው መስጂዱ "በዓለማችን የትኛውም ጥግ ከተገኙት ሁሉ ለየት ያለው ነው" ብለዋል።
የመስጂዱ ምዕመናኖችም የአካባቢው ገበሬዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን ግምት ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መስጂዱ ጣሪያ የሌለው ሲሆን፤ በአራት መአዘን ቅርፅ የታነፀ ነው። ፊቱን ወደ ሙስሊሞች ቅድስቷ ከተማ መካ ያዞረ መስገጃ አለው።
"ይህ የመስጂዱ አቀማመጥ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ሙስሊሞች በዚህ መስጂድ ውስጥ ይሰግዱ እንደነበር ምስክር ነው" ብለዋል የቅርስ ጥበቃ መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስልምና ታሪክን እንዳጠኑት ባለሙያዎች ከሆነ ይህ መስጂድ እስልምና ወደ አሁኗ እስራኤል በመጣበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተገነባ ቀደምት መስጂድ ነው ተብሎ ይታመናል።
አክለውም በዚያ ዘመን የነበረውን ሁኔታ የበለጠ ለማወቅ "የዚህ መስጂድ በአካባቢው መገኘት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው" ይላሉ።












