በበዴሳ ከተማ የ13 ዓመት ታዳጊን ህይወት ለማዳን የሞከሩ 4 ሰዎች የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ሞቱ

በበዴሳ ከተማ የ13 ዓመት ታዳጊን ህይወት ለማዳን የሞከሩ 4 ሰዎች የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Murti Mohammed

ትናንት እኩለ ቀን ላይ በምዕራብ ሃረርጌ ዞን በዴሳ ከተማ ውሃ ለመቅዳት የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ የቀረውን የ13 ዓመት ታደጊ ህይወት ለማትረፍ የሞከሩ 4 ሰዎችን ጨምሮ አምስት ሰዎች ህይወታቸው አለፈ።

የዓይን እማኞች እና የአከባቢው መስተዳደሮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቅድሚያ እስከ 22 ሜትር ጥልቀት ያለው እና ከኮንክሪት ወደ ተሰራው ጉድጓድ ውስጥ የ13 ዓመት ታዳጊው ከገባ በኋላ የእርሱን ህይወት ለማዳን በተደረጉ ጥረቶች ነው የተቀሩት የአራቱ ሰዎች ህይወት ያለፈው።

ጎረቤት እና አደጋው ሲከሰት በስፍራው የነበሩት የዓይን እማኝ ቱሬ ሃረር የተፈጠረውን እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።

"በመጀመሪያ የ13 ዓመቱ አራርሶ የሚባለው ልጅ ውሃ ለመቅዳት የውሃ ጉድዷ ውስጥ ገባ። ልጁ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ በመቅረቱ አጎቱ የሆነው ሌላ የ15 ዓመት ልጅ አራርሶን ለማውጣት ጉድጓድ ውስጥ ገባ። ሁለቱ ልጆች ገብተው ስለቀሩ ሌላ ሶስተኛ ሰው ልጆቹን አወጣለሁ ብሎ እሱም ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ እዛው ቀረ። ሰዎች ሲሞቱ ቆመን አናይም ብሎ ሌላ አራተኛው ሰው ገባ። እሱም ገብቶ ቀረ። እንደገና ሰዎቹን አድናለሁ ያለ አምስተኛ ሰው ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ የእርሱም ህይወት አለፈ።"

አቶ ረመዳን ሃሩን የበዴሳ ከተማ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲሆኑ በቅድሚያ ከኮንክሪት ወደተሰራው ጉድጓዱ ውስጥ የወደቀው ታዳጊ ለመስገድ ውሃ መቅዳት ፈልጎ እንደነበር ይናገራሉ።

አቶ ረመዳን በኤክስካቫተር በታገዘ ቁፋሮ የሟቾች አስክሬን ከስድስት ሰዓታት ጥረት በኋላ እንደወጣ ተናግረዋል።

"ጉድጓዱ ሲቆፈር እንዳየነው፤ በጉድጓዱ ውስጥ አንድ በርሜል እንኳን የማይሞላ ውሃ ነው ያየነው" ይላሉ የዓይን እማኙ አቶ ቱሬ። አቶ ረመዳንም "ምናልባት ሰዎቹ ህይወታቸው ያለፈው በኦክስጅን እጥረት ሳይሆን አይቀርም" ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ከሟቾቹ መካከል አራቱ ግለሰቦች የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው እና አምስተኛው ሰው ደግሞ የጋራዥ ሠራተኛ እንደሆነ አቶ ረመዳን ገልጸውልናል።

በከተማው የውሃ እጥረት መኖሩን ተከትሎ ሰዎች ከከተማው መስተዳደር ፍቃድ ውጪ የውሃ ጉድጓዶችን እንደሚቆፈሩ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊው ይናገራሉ።

ከዚህ በኋላ መሰል አደጋዎች እንዳይደርሱ ምን ታስቧል ለሚለው ጥያቄ አቶ ረመዳን ሲመልሱ፤ "በከተማዋው መሰል 20 ጉድጓዶች እንዳሉ ይገመታል። ጉድጓዶቹ እንዲዘጉ ወይም ሰዎች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት በሟሟላት ከውሃ ቢሮ ፍቃድ እንዲያገኙ ይደረጋል" ብለዋል።

የሟቾች የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ ተፈጽሟል።