በናይሮቢ የተደረመሰው ትምህርት ቤት ባለቤት ፍርድ ቤት ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሰኞ በኬንያ ናይሮቢ ተደርምሶ በተማሪዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው ትምህርት ቤት ባለቤት ፍርድ ቤት ቀረቡ።
በአደጋው 15 ተማሪዎች ሲሞቱ 67 የሚሆኑት ደግሞ በተለያየ ጉዳት ምክንያት የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
ሞሰስ ዋይናይና በትናንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የአደጋው ምክንያትም እስከሚጣራ በአቃቤ ህግ ጥያቄ መሰረት ለአስራ አምስት ቀናት ያህል በማረፊያ ይቆያሉ።
የትምህርት ቤቱን መደርመስ ተከትሎ የኬንያ የትምህርት ሚኒስቴር ፕሮፌሰር ጆርጅ ማጎሃ ፈቃዳቸውን እንዲሰረዝ እንዲሁም ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የናይሮቢ ገዢ ማይክ ሶንኮ በበኩላቸው አስራ ስድስት የሚሆኑ በናይሮቢ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎችን ከስራቸው አግደዋቸዋል።
ገዢው በአስተዳደሩ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ከግንባታ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠርና ችላ በማለት ይህንን አደጋ አስከትለዋልም በማለት ወንጅለዋቸዋል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ በመስፋፋት ላይ የነበረ ሲሆን ለዚህም የሚሆን ፈቃድ እንዳላገኘም ተጠቁሟል።












