ጅማ የከተመችውና ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ እና የሳይንስ እውቀት የምታንፀው ምሕረት

በዳይናሞ የቴክኖሎጂ ማዕከል ከሚማሩ ታዳጊዎች መካከል ጥቂቶቹ

የፎቶው ባለመብት, Dynamo center for technology

ቶታልኢነርጂስ ኢትዮጵያ የ2022 ሥራ ፈጣሪዎች በሚል ዘርፍ ያወዳደራቸውን ወጣቶች አሸናፊዎችን በቅርቡ አሳውቆ ነበር።

ድርጅቱ እድሜያቸው ከ18 እስከ 35 የሆኑ የተሻለ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማወዳደር ጥሪ ያቀረበው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።

ይህንን ጥሪ ተከትሎ ከ800 በላይ ተወዳዳሪዎች አለኝ የሚሉትን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ማስገባታቸው የተገለፀ ሲሆን 355 በሦስት የተለያዩ ዘርፎች ለውድድሩ ቀርበው ነበር።

እነዚህ ሦስት ዘርፎች ምርጥ የፈጠራ ፕሮጀክት፣ ምርጥ የሴት ሥራ ፈጣሪ እና ምርጥ በሦስት ዓመት ውስጥ ውጤታማ የሆነ የሥራ ፈጠራ በሚሉ ዘርፎች የተከፋፈሉ ነበሩ።

የውድድሩ አዘጋጆች 15 ወደ መጨረሻው የውድድሩ ምዕራፍ ያለፉትን በመምረጥ የፈጠራ ሥራቸውን እንዲያቀርቡ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት በምርጥ ሴት የሥራ ፈጣሪ ዘርፍ ምሕረት ይልማ ተመርጣ ተሸላሚ ሆናለች

የቶታል ኢነርጂስ ምርጥ ሴት የሥራ ፈጣሪዋ ምሕረት ማን ነች?

ምሕረት ይልማ ትባላለች። ከጅማ ዩኒቨርስቲ በባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች።

አሜሪካ ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ አይዋ ደግሞ በቢዝነስ፣ ሥራ ፈጣሪና፣ አመራር ዘርፍ ትምህርቷን አጠናቅቃ መመረቋን ትናገራለች።

ከሁለት ዓመት በፊት ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ዳይናሞ ሴንተር ፎር ቴክኖሎጂስ የተባለ ድርጀት በጅማ ከተማ መመስረታቸውን ለቢቢሲ ገልጻለች።

ይህ ማዕከል በጅማ ከተማ ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራም ይገኛል።

በዳይናሞ የቴክኖሎጂ ማዕከል ከሚማሩ ታዳጊዎች መካከል ጥቂቶቹ

የፎቶው ባለመብት, Dynamo center for technology

ምሕረት እና ጓደኞቿ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ያስተዋሉት ነገር ይህንን ድርጅት እንዲመሰርቱ ገፊ ምክንያት እንደሆናቸው ትናገራለች።

በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ወቅት የሚማሩትን የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ወደ ተግባር የመቀየር ችግር በማስተዋላቸው ይህንን ለመፍታት በማሰብ ድርጅቱን መስርተናል ትላለች።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ በነበሩበት ወቅት የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን ወደ ተግባር ለመቀየር የተከፈቱ ክፍሎች ቢኖሩም ነገር ግን "ደካማ" ነው ትላለች።

በዚህም ምክንያት ከዩኒቨርስቲ የሚመረቁ ወጣቶች የንድፈ ሃሳቡን እውቀት ጠንቅቀው ቢይዙትም ያላቸውን ሃሳብ ወደ ተግባር መቀየር ላይ ግን ቀርነት እንደሚስተዋልባቸው እርሷና ጓደኞቿ አስተውለዋል።

በተጨማሪም ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ጀምሮ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ እውቀት እየተኮተኮቱ እንዲያድጉ የሚል ዓላማን ሰንቀዋል።

እነዚህ የዛሬ ታዳጊዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሚገቡበት ወቅት ክህሎት ያላቸው፣ የሚፈልጉትን ሃሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ጉልበቱ እና ድፍረቱ የማያንሳቸው ብቁ ዜጎች እንደሚያደርጋቸው ትናገራለች።

ይህንን ሀሳብ ከጓደኞቿ ጋር ሆና ስትጀምረው በማዕከላቸው ለመማር ፈልገው የሚመጡ በየትኛውም የእድሜ እና የትምህርት ደረጃ የሚገኙትን ለመቀበል አስበውበታል።

በዚህም የተነሳ በአሁን ወቅት ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ጀምሮ እስከ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድረስ በማዕከላቸው ተገኝተው እውቀትና ክህሎት የሚቀስሙ መሆኑንም ታክላለች።

ምሕረት እና ጓደኞቿ ተማሪዎቹን በእውቀት እና ክህሎት ማስታጠቅ የሚያስችል ቤተ ሙከራ ለማቋቋም የገንዘብ ችግር እንቅፋት ከሆኑባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር።

ያቋቋሙት የፈጠራ ማበልፀጊያ ክፍል በበቂ ሁኔታ በሚያስፈልጉት ቁሳቁሶች እንዲደራጅ የወዳጅ ዘመድን እጅ ማየት፣ ብድር መጠየቅ እና በተለያዩ ጊዜ ያገኟቸው እና ያጠራቀሟቸውን ጥሪዎች መጠቀም ጠይቋቸው ነበር።

ከዚህ በኋላ ታዳጊዎቹ በቀላሉ ኤሌክትሮኒክስን የሚረዱበት፣ በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ምስል እና በድምጽ የታገዘ ትምህርት እየተማሩ፣ እየተዝናኑ የሚማሩበት፣ መቅረጻቸውንም ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገችበት ወቅት ተናግራለች።

ይህንን የቀረፁትን ማስተማሪያና ትምህርት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ ማስተማሪያቸውን በዚያ መልክ ማደራጀታቸውንም ጨምራ አክላለች።

ተማሪዎቹ ወደ እነርሱ ጋር በሚመጡበት ወቅት በአማርኛ እና በኦሮምኛ እንዲማሩ አድርገው ማስተማርያዎቻቸውን አዘጋጅተዋል።

በማዕከሉ ውስጥ ትምህርት ሲሰጡም በእድሜ እና በክህሎት ደረጃ በመከፋፈል ያሰለጥናሉ።

ምሕረት ከቶታልኢነርጂስ ሽልማቷን ስትቀበል

የፎቶው ባለመብት, Dynamo center for technology

የዳይናሞ ሴንተር ፎር ቴክኖሎጂስ ተማሪዎች

ይህ ማዕከል ጅማ ከትሞ ሳይንስን ለታዳጊዎች ቅርብ ለማድረግ ይተጋል።

ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ያስተምራል። ትንንሽ ተመራማሪዎችን ፈጣሪዎችን ደግሞ እንደ ፍላጎታቸው ልክ እና መልክ ያግዛል።

ይህ ማዕከል በዋናነት በሮቦቲክስ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በፕሮግራሚንግ ተማሪዎቹን ያሰለጥናል።

ከቤተሰብ በብድር መልክ በተሰበሰበ ገንዘብ የተመሰረተው ይህ ማዕከል በአሁኑ ጊዜ 12 ባለሙያዎችንን ቀጥሮ ያሰራል።

ወደ ማዕከሉ መጥተው የሚማሩ ተማሪዎችን ተመጣጣኝ የሚባል ክፍያ ያስከፍላሉ።

ተማሪዎቹ በንድፈ ሃሳብ የሚማሩትን እያዩ እየዳሰሱ እንዲማሩ ለማድረግ እንዲያስችላቸው ለታዳጊዎች የሚሆን ቀለል ያለ ዲጂታል ማስተማርያ መሳሪያ ራሳቸው ማዘጋጀታቸውን ምሕረት ትገልጻለች።

ይህ ዲጂታል ማስተማርያ ደግሞ ለተማሪዎቹ የሚመጥን ነው አይደለም የሚለውን ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች ላይ ፍተሻ ማድረጋቸውን ገልጻለች።

በተለይ ፕሮግራሚንግ ትላለች ምሕረት፣ ብዙዎች ከባድ መሆኑን እንደሚያስቡ ነገር ግን ተማሪዎቻቸው ቀላል በሆነ እና ዘና እያሉ የሚማሩበትን መንገድ እንደሚከተሉ ታብራራለች።

እነዚህ ታዳጊዎች ፕሮግራሚንግ ሲማሩ ጌሞችን እና ሮቦቶችን እንደምን አድርገው ማበልፀግ እንደሚችሉ እየተዝናኑ እና የፈጠራ ንቃተ ሕሊናቸውን እያዳበሩ እንዲማሩ ይደረጋል።

በዚህ ማዕከላቸው የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሚያበለጽጉ የምትናገረው ምሕረት፣ በአነስተኛ መሬት ላይ ሰብል ለሚያመርቱ ገበሬዎች የሰሩት ትራክተር መኖሩንም ለቢቢሲ ገልጻለች።

በአነስተኛ መሬት ላይ የሚያመርቱ ገበሬዎች በቀላሉ ምርታማነታቸውን ለመጨመር የሚያስችላቸው ትራክተር በመስራት ከጅማ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ወደ ተግባር ለመግባት የሚቻልበትን ሁኔታ እየፈተሹ ይገኛሉ።

ዳይናሞ ሴንተር ፎር ቴክኖሎጂስ እስካሁን ድረስ በሁለት ዙር ያስተማራቸውን 1180 ተማሪዎች ማስመረቁን ምህረት ታክላለች።

የሁለተኛ ዙር ተማሪዎቻቸውንም ባስመረቁበት ወቅት የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ እና ፌስቲቫል በማዘጋጀት ለጅማ ዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ እና ለከተማዋ ነዋሪዎች አሳይተዋል።

በዚህም ማዕከሉ ውስጥ የተሰሩ ጌሞች፣ ሮቦቶች እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

እነዚህ ተማሪዎቻቸው ከመደበኛ ትምህርት ሰዓታቸው ውጪ ትምህርቱን እንዲያገኙ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የምታስታውሰው፣ ምሕረት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ መደበኛ ትምህርት ሲቋረጥ ደግሞ የተማሪዎቹን ቁጥር በመቀነስ እና በሰዓት በመከፋፈል በመደበኛ ሰዓቶች ሲያስተምሩ ቆይተዋል።

ዌብ ሳይት ዴቬሎፕመንት፣ ሳይበር ሴክዩሪቲ፣ ፕሮግራሚንግ፣ ግራፊክ ዲዛይኒንግ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ክህሎቱ እንዲኖራቸው ለሚፈልጉ የሚያስተምሯቸው ክህሎቶች ናቸው።

በዳይናሞ የቴክኖሎጂ ማዕከል ከሚማሩ ታዳጊዎች መካከል ጥቂቶቹ

የፎቶው ባለመብት, Dynamo center for technology

ታዳጊዎቹ ወዳሉበት መሄድ

ምሕረት በመንግሥትም ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ወደ እነሱ ማዕከል ሳይመጡ የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን እና ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት እቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር መግባታቸውን ትናገራለች።

ይህንንም በጅማ ከተማ በሚገኙ ስድስት የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጋር በመነጋገር እየሰሩ ነው።

በተለይ ከሦስት ትምህርት ቤቶች ጋር በመነጋገር እና በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ በማቋቋም የእቀውቀት ሽግግሩን መጀመራቸውን ታስረዳለች።

በእነዚህ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ ክፍለ ጊዜ እንዲኖራቸው በማድረግ ወደ ላቦራቶሪው በመምጣት መሰረታዊ እውቀታቸወን የሚያዳብሩበትን ሥራ ጀምረዋል።

ትምህርቱ በማዕከሉ መምህራን እንደሚሰጥ የምትናገረው ምሕረት፣ ስለ ስፔስ ሳይንስ፣ ስለቴክኖሎጂ፣ ስለ ሮቦቲክስ፣ ፕሮግራሚንግ ያስተምራሉ።

ይህንን በማድረጋቸው ወደ ማዕከላቸው መጥተው መማር ያልቻሉ ታዳጊዎች የመማር እድልን እንደሰጣቸው ለእነርሱም የተደራሽነት አድማሳቸውን ማስፋቱን ትገልጻለች።

"የኔ ተማሪዎች ራሴን ያስገርሙኛል" የምትለው ምሕረት በሥልጠናው ወቅት ችግርን መለየት እና ሥራ ፈጠራ የተሰኙ ሥልጠናዎች አብረው ስለሚወስዱ የተማሩትን እውቀት ወደ ተግባር ለመቀየር በአካባቢያቸው የሚገኝን ችግር በመመልከት የመፍትሔ ሃሳብ እንዲያመነጩ እንደሚያግዛቸው ትናገራለች።

ይህንን ትምህርታቸውን በመጠቀምም ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ እና ተፈላጊውን የጥራት ደረጃ በሚጠብቅ መልኩ ቡና የሚፈለፍል ማሽን የሰሩ ታዳጊዎች፣ አሽከርካሪዎች ለሊት በሚያሽከረክሩበት ወቅት እንቅልፍ እንዳይጥላቸው ከሚያግዝ እና የአይን እርግብግቢትን በመቁጠር የማንቂያ ደወል የሚያሰማ መነጽር የሰሩ ተማሪዎች አሏቸው።

በዳይናሞ የቴክኖሎጂ ማዕከል ከሚማሩ ታዳጊዎች መካከል ጥቂቶቹ

የፎቶው ባለመብት, Dynamo center for technology

ልጆች ትልቅ አቅም አላቸው የምትለው ምሕረት ወደፊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ቅርንጫፎችን መክፈት ሃሳብ እንዳላት ገልጻለች።

ምሕረት ቶታልኢነርጂስ ባዘጋጀው ውድድር በማሸነፏ 370 ሺህ ብር ሽልማት አግኝታለች።

ከዚህ በተጨማሪ ሥራቸውን በተሻለ አቅም መስራት የሚያስችላቸው ሥልጠናዎችን እንደሚያገኙ ተገልጿል።

በመጪው ሳምንታት ደግሞ ከ32 የአፍሪካ አገራት ከተውጣጡ እና የቶታልኢነርጂስ የፈጠራ ሥራ ውድድር አሸናፊዎች ከሆኑ ተወዳዳሪዎች ጋር ለመፋለም ኢትዮጵያን ወክላ ወደ ፈረንሳይ ትሄዳለች።