ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በተባበሩት መንግሥታት የሚመራው የሱዳን ድርድር ተቃውሞ ገጠመው
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመራው የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለተኛ ዙር ድርድር በዛሬው ዕለት እንዲጀመር እቅድ የተያዘለት ቢሆንም መከፋፈሎች አጋጥመዋል።
በጥቅምት ወር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ባለመው ድርድር ላይ እንደማይሳተፉ በርካታ ፓርቲዎች እየገለጹ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጥምረት በአገሪቱ ያሉትን ወታደራዊ ኃይል፣ የዲሞክራሲ ተሟጋቾች እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማደራደር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
በድርድሩ አንገኝም ካሉት መካከል የሱዳን ባለሙያዎች ማህበር (ኤስፒኤ)፣ የሱዳን ኮሚኒስት ፓርቲ (ኤስሲፒ) እና የሱዳን ኮንግረስ ፓርቲ (ኤስኮፒ) ይገኙበታል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይቱን "ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱን ህጋዊ ለማድረግ የተደረገ ሙከራ ነው" ሲሉ ሌሎች ደግሞ በይፋ አልተጋበዝንም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
አሜሪካ ሁሉም የአገሪቱ ሲቪል እና ወታደራዊ አካላት በተባበሩት መንግሥታት የሚመራውን ድርድር በመደገፍና ይህንንም ሂደት በመጠቀም ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እና ብሄራዊ መረጋጋትን እንዲያመጡ አሳስባለች።
"በሱዳን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማምጣትና የሲቪል አመራሩን ወደነበረበት ለመመለስ እየተደረገ ላለው ጥምር ጥረት ጠንካራ ድጋፍ ታደርጋለች" ብሏል ከአሜሪካ በኩል የተሰጠው መግለጫ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ100 የሚበልጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የወጣቶች እና የሴቶች ቡድኖች የሱዳንን ሉዓላዊነት እንዲከበር የሚጠይቅ ሰነድ ትናንት ሰኞ ፈርመዋል።
በዋናነት የወታደራዊ ኃይሉ ደጋፊ የሆኑት እነዚህ ቡድኖች በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ "የውጭ ጣልቃ ገብነት" እንደማይቀበሉ እና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሾሙ ጠይቀዋል።