ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምዕራብ ኦሮሚያ ባለው ሰብዓዊ ቀውስ ሳቢያ ቢያንስ 500 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ
በምዕራብ ኦሮሚያ እየተባባሰ በመጣው ሰብዓዊ ቀውስ ሳቢያ ቢያንስ 500 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) እንደገለጸው በክልሉ ባለው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ካማሺ ዞን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ጨምሮ 500 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ቀያቸውን ለቀው ወጥተዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የጸጥታ መናጋት በዚህ ዓመት ተባብሶ መቀጠሉን የገለፀው ሪፖርቱ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ካማሺ ዞን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአንድም ሁለት ሦስቴ መፈናቀላቸውን አመልክቷል።
እርዳታ ሰጪዎች በዚህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ድጋፍ ለማድረግ ጥረታቸውን ቢቀጥሉም፣ የችግሩ አሳሳቢነት እየጨመረ መምጣቱን ተቋሙ ገልጿል።
ኦቻ እንደሚለው ከዚህ ቀደም ሁለት የተራድኦ ሠራተኞች ተተኩሶባቸዋል። የሠራተኞች ትንኮሳን፣ እገታን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል።
የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት መከላከል ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ገረመው ኦሊቃ ከምዕራብ ወለጋ 11 ሺህ ሰዎች፣ ከምስራቅ ወለጋ ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ገልጸዋል።
የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ኃይል ከለላ እየሰጠ እርዳታ ለማድረግ እየሞከረ እንደሆነም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ሄደው ለመስራት እንደሚቸገሩ የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ በመንግሥት ደረጃ ግን በተለይ እናቶችና ህጻናት ለአደጋ እንዳይጋለጡ የማድረግ ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እንደ ጸጥታ ሁኔታው እንደሚለያይና ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ እንደሌሉም ገልጸው፤ ግጭት ሸሽተው በተለያዩ ቦታዎች የተጠለሉ ሰዎችን ለመታደግ በያሉበት የነፍስ አድን ሥራ እየሰራን ነው ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የምዕራብ ኦሮሚያ ክፍል ሰዎች በግፍ የሚገደሉበት፣ የሚፈናቀሉበት እና ንብረት የሚወድምበት አካባቢ ሆኖ እስካሁን ቀጥሏል።
በምዕራብ ኦሮሚያ በ2013 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በተከታታይ ለቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በታጣቂዎች መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።
በአካባቢው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለሚፈፀመው ግድያ እና ማፈናቀል መንግሥት 'ሸኔ' የሚለውን እና ራሱን 'የኦሮሞ ነጻነት ጦር' ብሎ የሚጠራውን ቡድን እንዲሁም በአጎራባች ክልሎች ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ይከሳል።
ይህንንም ተከትሎ ሰላም ለማስፈን መንግሥት ታጣቂ ቡድኑን " ሸኔ" ለማጥፋት ዘመቻ መጀመሩን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። በዘመቻውም ታጣቂ ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ ግን መንግሥት ድል እየቀናው ሳይሆን ሰላማዊ ሰዎችን እየገደለ ነው ሲል አስተባብሏል።
የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት መከላከል ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ገረመውም ለዚህ ዋነኛው መፍትሔ መንግሥት በጀመረው ዘመቻ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኦቻ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢ የሚነሳው ተደጋጋሚ ግጭት ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ሲሆን በተለይም በቄለም ወለጋ ዞኖች በጸጥታ ኃይሎችና ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ የተራድኦ ሥራን ማደናቀፉን ቀጥሏል።
ወደ ምሥራቅና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እንዲሁም ሰሜን፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምሥራቅ ሸዋ የተስፋፋው ግጭት ነዋሪዎች ከኦሮሚያ ወደ አማራ ክልል እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
የሰብዓዊ እርዳታ ሥራውም መተላለፊያ መንገድ በማጣት፣ በቂ በጀት ባለመኖሩ እና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች እንደሚደናቀፍ የኦቻ ሪፖርት ጠቁሟል።
በእርዳታ መስተጓጎል ሳቢያ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የገጠማቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ቁጥር 22 በመቶ መጨመሩ የጨመረ ሲሆን ቁጥሩ በነፍሰ ጡር ሴቶችና እናቶች ዘንድ 42 በመቶ ከፍ ብሏል።
በጸጥታ እጦት ምክንያት አልሚ ምግቦችን ማከፋፈል እንዳልተቻለ ኦቻ ጨምሮ ገልጿል።
በተለይም ወደ ገጠራማ አካባቢዎች እርዳታ ለማድረስ እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ያመለከተው ሪፖርቱ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና በካማሺ ዞን በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ አልተቻለምም ብሏል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በምዕራብ ኦሮሚያ በዝርፊያና ውድመት ሳቢያ 426 የጤና ተቋማት አገልግሎት አይሰጡም።
በምሥራቅ ወለጋ 144 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን 62 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል። በምዕራብ ወለጋ ደግሞ 184 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው 89 ሺህ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ አይገኙም።
"መንገድ ስለሚዘጋም ነዋሪዎች ወደ ገበያ መሄድ አይችሉም። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ግብአት ለማግኘት ይቸገራሉ" ብሏል ኦቻ በሪፖርቱ።
በምዕራብ ኦሮሚያ ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ እንደመጣም ሪፖርቱ ጠቁሟል።