የቢትኮይን ዋጋ በ50 በመቶ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆለቆለ

ዋጋው እያሽቆለቆለ ያለው ቢትኮይን፣ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቅናሽ በማሳየት አንድ ቢትኮይን 34ሺህ የአሜሪካ ዶላር እየተሸጠ ነው።

የክሪፕቶከረንሲ አሻሻጩ ኮይንቤዝ ከስድስት 6 ወራት በፊት ጣራ ነክቶ የነበረው ቢትኮይን በአሁኑ ወቅት ዋጋው 50 በመቶ ቀንሷል ብሏል።

በክሪፕቶከረንሲዎች የገበያ ድርሻ ቀዳሚ የሆነው ቢትኮይን ዋጋው መቀነሱ የተሰማው በመላው ዓለም የድርሻ ገበያዎች [ስቶክ ገበያ] መቀነሳቸውን ተከትሎ ነው። የክሪፕቶካረንሲዎች ዋጋ ከዓለም የስቶክ ገበያ ጋር ተያይዞ ዋጋቸው ከፍ እና ዝቅ ሲል ይስተዋላል።

በ650 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ ዋጋ ቢትኮይን የዓለማችንን አንድ ሦስተኛ የክሪፕቶከረንሲ ጠቅላላ ድርሻ ይይዛል።

በአሁኑ ወቅት ቢትኮይን በአንዳንድ አገራት ጨምር ይፋዊ መገበያያ እየሆነ ነው። በቅርቡ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያ ያደረገች ሲሆን ቢትኮይንን አገር አቀፍ መገበያያ በማድረግ ኤል ሳልቫዶር የመጀመሪያዋ ናት።

ኤል ሳልቫዶር ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያ ስታደርግ አይኤምኤፍን ጨምሮ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ውሳኔውን ተችተው ነበር።

ግብይት ለመፈጸም ክሪፕቶከረንሲዎች ለግለሰቦች የሚሰጡት ነጻነት እንዳለው ሁሉ፤ ክሪፕቶከረንሲዎች በሕገ-ወጥ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብ ያስችላሉ።

በተጨማሪም ክሪፕቶከረንሲን በመጠቀም አፍራሽ ተልዕኮዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ይቻላል እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓት አለመረጋጋትን ይፈጥራል በሚሉ ምክንያቶች ሥርዓቱ ይተቻል።

ከቢትኮይን ቀጥሎ ትልቁን የገበያ ድርሻ የሚይዘው ኢቲሪየም በተመሳሳይ ባለፉት ቀናት ዋጋው ከ10 በመቶ በላይ ቀንሷል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ባንኮች የዋጋ ግሽበተን ለመቆጣጠር በሚል የወለድ መጠንን ከፍ አድርገው ነበር።

ይህም ተበዳሪዎች ብድር የሚወስዱበትን የወለድ መጠን ከፍ አድርጓል።

በርካታ ኢንቨስተሮች የዋጋ ግሽበት እና የብድር ወለድ መጠን ከፍ ማለት በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል።