ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ከሰሞኑ በተከሰቱ የሃይማኖት ግጭቶች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ተመድ ጠየቀ
በኢትዮጵያ በቅርቡ በተከሰቱ የሃይማኖት ግጭቶች ላይ መንግሥት ገለልተኛ ግልፅና ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ጠየቀ።
ከሰሞኑ በሙስሊሞችና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች ቢያንስ 30 ሰዎች መሞታቸውና እንዲሁም ከ100 በላይ ግለሰቦች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት በትናንትናው ዕለት ሚያዝያ 29፣ 2014 ዓ.ም በወጣው መግለጫቸው ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ ሚያዝያ 18፣ 2014 ዓ.ም በቀብር ስነ ስርዓት ላይ ከመካነ መቃብር ውዝግብ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ከ150 በላይ ሰዎችም ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለፁ ይታወሳል ።
በጎንደር የተነሳውንም ግጭት ተከትሎ ሁኔታው በተለያዩ ክልሎች ወደሚገኙ ከተሞችና ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የተዛመተ ይመስላል ብለዋል ኮሚሽነሯ በተቋማቸው ድረ-ገፅ ባሰፈሩት መግለጫ።
በጎንደር ሁለት መስጊዶች እንደተቃጠሉና ሁለቱ ደግሞ በከፊል መውደማቸውን መረዳታቸውንም ኮሚሽነሯ በዚሁ መግለጫቸው አስፍረዋል።
የጎንደሩንም ግጭት ተከትሎ በተከሰቱ አጸፋዊ ጥቃቶች በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ሁለት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑ ግለሰቦች በእሳት ተቃጥለው እንዲሁም አንድ ግለሰብ ተደብድቦ መገደላቸውንና አምስት ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጥለዋል ብለዋል።
በደባርቅ እንዲሁም በአፋር ክልልና ድሬዳዋ ተጨማሪ ሁከት መኖራቸውንም አስፍረዋል።
በደባርቅ ከተማ ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ.ም ሁለት መስጅዶች እንደተቃጠሉ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለፁ ይታወሳል።
ለሰዎች ህይወት መጥፋትና፣ ለእምነት ተቋማት መውደም ጥፋተኛ የሆኑ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃም እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከነዚህ ሁከቶች ጋር በተያያዘ ቢያንስ በአራት ከተሞች ከ578 የማያንሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ማስታወቁም በመግለጫው ሰፍሯል
በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦችም የፍርድ ሂደታቸው ያለ አድልዎና የአለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ህግ መሰረት በተከተለ መልኩ ፍትሃዊ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
በሃይማኖቶች መካከል ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከልም መንግሥት ተጎጂ ህበረሰቦችንና ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦችን ትርጉም ባለው መልኩ ባሳተፈ መልኩ ለነዚህ ሁከቶች መፍትሔ መሰጠት እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጎንደርና ሌሎች ከተሞች ላይ ከተነሱ ግጭቶች በተጨማሪ ሚያዝያ 24 ዕለት በአዲስ አበባም በኢድ ሰላት ወቅት ግርግር ተነስቶ የነበረ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የተባሉ 76 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መገለፁ ይታወሳል።
በዚህም ሁከት በጸጥታ አካላት ላይ የአካል ጉዳት እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይም ጉዳት ደርሷል ተብሏል።