ከጎንደሩ ግጭት በኋላ በሌሎች አካባቢዎች በሃይማኖት ተቋማት ላይ ውድመት ደረሰ

ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ።

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመስጅድ እና የዕውቀት ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዑስማን ዑመር ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ትላንት ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ. ም. በደባርቅ ከተማ ሁለት መስጅዶች እንደተቃጠሉና ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደሞቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በደቡብ ክልል፣ ስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ ትላንት ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ. ም. ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች ላይ ውድመት እንደደረሰ የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከውድመቱ በተጨማሪ በሰዎች ላይ ጉዳት ድብደባ መፈጸሙን መግለጫው አክሏል።

በስልጤ ዞን ምን ተከሰተ?

የሃዲያ እና ስልጤ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ፣ ትላንት በስልጤ ዞን ከተቃጠሉት ሁለት አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪም ተጨማሪ አንድ ገዳም መቃጠሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መላከሕይወት ቀሲስ ንጉሤ፣ ዞን ምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የምትገኘው ፍኖተ ለዛ ቅድስተ ማርያም ገዳም ሚያዚያ 20፣2014 ዓ. ም. እኩለ ለሊት ላይ እንደተቃጠለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ "ሕዝበ ሙስሊሙ ከሰላት ሲወጡ መፈክር በመያዝ፣ የወራቤ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ጉልላቱ ወርዶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ ተቃጥለዋል። ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ ፈራርሷል። አገልጋዮችና የጥበቃ ሠራተኞች ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸዋል" ብሏል።

በተጨማሪም የሳንኩራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን "በአክራሪ ኃይሎች" ሙሉ በሙሉ በእሳት ቃጠሎ መውደሙን ጽሕፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከአገረ ስብከቱ ያወጣው መግለጫ፣ በስልጤ ዞን ውስጥ ያሉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት "ከፍተኛ ጫና ውስጥ በመሆናቸው እርዳታና ጥበቃ ይደረግላቸው" ሲል ጠይቋል።

ከደረሰው የአካል ጉዳትና ውድመት ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሆኑ ለሕግ እንዲቀርቡም የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ጠይቋል።

በደባርቅ ምን ተከሰተ?

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመስጅድ እና የዕውቀት ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዑስማን ዑመር፣ በደባርቅ ከተማ ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደሞቱና ሁለት መስጅዶች እንደተቃጠሉ ገልጸዋል።

በደባርቅ ከተማ ጉዳቱ ያጋጠመው በአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሏል የሚል መረጃ ከወጣ በኋላ መሆኑን ሐጅ ዑስማን ተናግረዋል።

"መነሻ ምክንያት እየተፈለገ ነው እንጂ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሊላከክ የሚችል ችግር የለም" ብለዋል።

የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን፣ የሰሜን ጎንደር ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ዋቢ አድርጎ፤ ትናንት ሚያዚያ 20፣ 2014 ዓ.ም. በደባርቅ ከተማ በምትገኘው የጎጢት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ የተፈጠረዉ "መጠነኛ የጸጥታ ችግር ወደ ነበረበት ሰላምና መረጋጋት ተመልሷል" ብሎ ነበር።

ምን እርምጃ ተወሰደ?

ማክሰኞ ሚያዚያ 18፣ 2014 ዓ. ም. በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በሁከቱ እጃቸው አለበት የተባሉ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌደራሉ መንግሥት አስታውቋል።

ትናንት ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ. ም. የፌደራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል ብሏል።

በመግለጫው በጎንደር ከተማ በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰውን ግጭት መነሻ በማድረግ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ተብሏል።

ይህ የግብረ ኃይሉ መግለጫ የተሰማው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) "ክልሉን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ የሽብር ድርጊት በሚፈጠሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን" ካሉ በኋላ ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ ትናንት በክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባስላለፉት መልዕክት በጎንደር ከተማ ያጋጠመውን ክስተት አውግዘው አስተዳደራቸው ጥፋተኞች ለፍርድ እንደሚያቀርብ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ በትዊተር ገጻቸው "ማንንም ለማጥፋት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ጥቃት በሁላችን ላይ የሚደረግ ነው። አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥቃት ለማባባስ መሞከር የለብንም" ብለዋል።

በጎንደሩ ግጭት ቢያንስ 20 ሰዎች መሞታቸውን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገልጿል።