በለንደን በሕግ ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ ሠራተኞች በደመወዝ ቅናሽ በቋሚነት ከቤት እንዲሠሩ ፈቀደ

በለንደን የሚገኝ እና በሕግ ዘርፍ የሚሰራ አንድ ኩባንያ ሠራተኞች በቋሚነት ከቤት የሚሰሩበትን አማራጭ ይፋ አድርጓል። ሆኖም ይህንን አማራጭ የሚወስዱ ሠራተኞች ሙሉ ደመወዛቸውን አያገኙም።

በለንደን የሚገኘው ስቴፈንሰን ሃርውድ የተባለው በሕግ የሥራ ዘርፍ ላይ የታወቀ ስም ያለው ድርጅት ያስቀመጠውን በቋሚነት ከቤት የመስራት አማራጭ የሚፈልጉ ሰዎች ከደመወዛቸው 20 በመቶው ይቆረጣል።

የኮሮና ወረርሽኝ ይዟቸው ከመጡ ጉዳዮች አንዱ ከቤት መስራትን ነው። ሆኖም ከቤት መስራት ማንን ይጠቀማል? ማንን ይጎዳል? በሚል ሲያከራክር ቆይቷል።

ከቤት በመስራት አሰሪም፣ ሠረተኛም እየተጠቀሙ ነው። ሠራተኞች ገንዘብ እና ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ ሲያግዝ አሰሪዎችን ደግሞ ለቢሮ ቦታ እና ሥራ ማስኬጂያ የሚያወጡትን ወጪ ቀንሷል።

ሆኖም ሠራተኞች ከቤት ሲሰሩ የሚሰሩበት መጠን ወይም ምርታማነታቸው ዝቅ ይላል በሚል የሚከራከሩም አሉ።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ሰዎች ወደ ሥራ ቦታቸው ለመሄድ የሚያጠፉትን ጊዜ በመቆጠብ በምሽት እና በእረፍት ሰዓት ብዙም ሳይረበሹ እንዲሰሩ ያስችላል የሚሉም አሉ።

በቅርቡ በዩኬ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ የሆኑት ጃኮብ ሪስሞግ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ከቤት መስራቱን ያቁም ማለታቸውን ተከትሎ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።

በጉዳዩ ላይ በትምህርት ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች ከቤት መስራት የሠራተኞችን ውጤታማነት ከፍ እንደሚያደረግ ያሳያሉ። በርካታ የግል ኩባንያዎች ደግሞ ከቤት እና ከቢሮ እያቀያየሩ ማሰራት ሰፋ ያለ የሥራ ቦታ እንዲኖር እንደሚያስችል እና ሠራተኞችንም እያስደሰተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስቴፈን ሃርውድ የኮሮና ወርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ ከቤት የሚሰሩ እና ከለንደን ውጪ ያሉ ሠራተኞችን በዝቅተኛ ደመወዝ መቅጠር መቻሉን ለቢቢሲ ገልጿል።

ሆኖም እነዚህ ሠራተኞች ከቢሮ መስራት ቢፈልጉ የመጓጓዣ ወጪ መጠየቅ እንደሚችሉ ተናግሯል።

የስቴፈን የሕግ ኩባንያ አሁን ያቀረበው አማራጭ ያላቸው ሠራተኞች ከቤት ለመስራት ማመልከት እንደሚችሉ ያስታወቀ ሲሆን ከቤት እና ከቢሮ የሚሰሩ ሰዎች በሁለት ዓይነት የደመወዝ ማዕቀፍ የሚሰሩበትን አሰራርም ዘርግቷል።

በአጋርነት ከሚሰሩት ውጪ ሁሉም ሠራተኞች ቢሮ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ካሉበት የመስራት አማራጭ ተሰጥቷቸዋል።

ኩባንያው ብዙ ሠራተኞች ከቤት የመስራት አማራጭን ይወስዳሉ ብሎ እንደማይጠብቅም ገልጿል። በዚህ አሰራር መሰረት ለድርጅቱ የተቀጠረን አንድ ሠራተኛ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ደመወዙ 90 ሺህ ፓውንድ ቢሆን ከቤት ለመስራት ቢወስን ደመወዙ ወደ 72 ሺህ ፓውንድ ዝቅ ይላል ማለት ነው።

አሁን ላይ ሠራተኞች በሳምንት እስከ ሁለት ቀን መስራት የሚችሉበት አማራጭ የተዘረጋ ሲሆን ይህ ቤት ከቤት እና ቢሮ እየቀያየሩ የመስራት አሰራር በድርጅቱ ሥር ላሉ በለንደን ፣ ፓሪስ ፣ ግሪክ ፣ ሆንግኮንግ ፣ ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያ ለሚገኙ 1 ሺህ 100 ሠራተኞች እየተተገበረ ነው።

"ለአብዛኛው ሠራተኞቻችን ይህ ፖሊሲያችን በአግባቡ እየሰራ ነው" ሲሉም የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ኒኮላስ ብሉም ከኮሮና ወርርሽኝ ማክተም በኋላ 10 በመቶ የሚሆነው ሠራተኛ ከቤቱ ይሰራል የሚል ግምት አስቀምጠዋል።

እንደሳቸው ገለጻ ከሆነ ከቤት መስራት የሠራተኞችን ውጤታማነት ለመጨመር፤ እኩልነትን መሰረት ያላደረገን አሰራር ለማጥበብ እና ከበድ ያለ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች በተሻለ ነጻነት እንዲሰሩ ያግዛል።

የተወሰኑ ተቋማት ሠራተኞች በተቀየጠው አሰራርም ቢሆን ወደ ቢሮ መመለስን እየተቃወሙ ይገኛሉ። አፕል በሳምንት ሦስት ቀን ከቢሮ ለመስራት ያቀደ ሲሆን ይህ አሰራሩ ተቋሙን "የወጣቶች፣ የነጮች እና የወንዶች የበላይነት" የሚታይበት ያደርገዋል የሚል አስተያየት ቀርቦበታል።