የአፋር ክልል የትግራይ ኃይሎች ከክልሉ ሙሉ በሙሉ አልወጡም አለ

የአፋር ክልል የትግራይ ኃይሎች ከክልሉ ግዛት ሙሉ በሙሉ አልወጡም አለ።

የአፋር ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም ሁመድ መሐመድ የትግራይ ኃይሎች ከአብዛኛው የክልሉ ስፍራ ቢወጡም ሙሉ በሙሉ ግን ከክልሉ ግዛት አልወጡም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡና ለሚመለከተው ሁሉ በሚል ባስተላለፉት መልዕክት"በአፋር ክልል የቀረ አንድም የትግራይ ኃይል የለም" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የአፋር ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም ሁመድ መሐመድ፤ "ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አልወጡም። መጋሌ ወረዳ ውስጥ አራጁ እና ሂዳ የሚባሉ ቀበሌዎች ላይ የተወሰነ ሠራዊት አለ (የህወሓት)። ከአባላ 15 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የኛ ድንበር ውስጥም እስካሁን አሉ።" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ኢብራሂም ገለጻ ባለፉት ሦስት ቀናት የትግራይ ኃይሎች ከአብዛኛው የአፋር ክልል መውጣት ጀምረዋል። "በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ከአብዛኛው ቦታ ለቅቀው ወጥተዋል። ከበርሃሌም ከትናንት በስቲያ [ሚያዚያ 16/2014 ዓ.ም] ነው የወጡት" ብለዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ሠራዊትን ከአፋር ክልል ማስወጣት ያስፈላጋቸው የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ ክልል እንደ ልብ ሊገባ ይችላል የሚል ተስፋ ስላላቸው መሆኑን ሮይተር በዘገባው አስፍሯል።

"ሠራዊታችን መላውን አፋር ለቅቆ ወጥቷል" በማለት አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ከሳምንታት በፊት የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ ክልል ለማድረስ በሚል ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥት የሰብዓዊነት የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ ህወሓት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል።

ህወሓት ሠራዊቴን ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ አስወጥቻለሁ በሚለው ጉዳይ ላይ የፌደራሉ መንግሥት

እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።

ይሁን እንጂ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ከሶስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የትግራይ ኃይሎች ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ ጠይቆ ነበር።

በዚሁ መግለጫ ላይ ወደ ትግራይ የሄዱና ያልተመለሱ 1025 የጭነት መኪኖች እንዲመለሱና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግም የፌደራሉ መንግሥት ጠይቋል።

ከቀናት በፊት ህወሃት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለመውጣት ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ አሰራር መዘርጋትና የተቋረጡ መሰረተ ልማት አገልግሎቶች መመለስን ጨምሮ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል።

በወቅቱም እንደ ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀመጡት መካከል ለትግራይ ህዝብ ወሳኝ የሆነው ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ አስተማማኝ መተላለፊያዎች (ኮሪደሮች) መኖር፣ ዘላቂ፣ ያልተገደበ፣ ወቅታዊ እና በቂ የሆነ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንዲሁም በትግራይ የተጣለው እገዳ ተነስቶ አስፈላጊው የማህበራዊ ኢኮኖሚ አገልግሎት መመለስ እንዳለበት የህወሃት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረው ነበር።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች ተቋርጠው ይገኛሉ።

የትግራይ ኃይሎች በአፋር

የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ ወረዳዎችን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ነበር።

ከዚህ ቀደም የአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ኻሎይታ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን ተናግረው ነበር።

በኪልበቲ ረሱ ዞን በህወሓት ቁጥጥር ሥር ገብተዋል ተብለው ከነበሩት 5 ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲ እና በራህሌ ይገኙባቸዋል።

ከሰሞኑ ህወሃት ሰራዊቱን ኢሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው የአፋር ክልል አስወጥቻለሁ ያለ ሲሆን ከዚህም ውሳኔ ላይ የደረሰው ለሰብአዊነት ሲባል የተደረሰው ስምምነት ተከብሮ ያልተገደብ ሰብአዊ እርዳታ ትግራይ እንዲደርስ ነው ማለቱ ይታወሳል።

የተኩስ አቁሙ ከታወጀ በኋላ የትናንትናውን ጨምሮ የደረሰው 144 የእርዳታ መኪኖች መሆናቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም መረጃም የሚጠቁም ሲሆን እርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መድረስ አልተቻለም ተብሏል።

በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ እርዳታ ተቋርጦ ስለቆየ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን ቦስስት እጥፍ አድጎ፣ 300 መኪኖች በቀን እንዲገባ ከተራድኦ ድርጅቶቹ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ከሰሞኑ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ኪሳራ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።