ህወሓት ሠራዊቴን ከአፋር ሙሉ በሙሉ አስወጥቻለሁ አለ

የትግራይ ኃይሎች ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን የህወሃት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

አቶ ጌታቸው በተጨማሪም በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡና ለሚመለከተው ሁሉ በሚል ባስተላለፉት መልዕክት"በአፋር ክልል የቀረ አንድም የትግራይ ኃይል የለም" ብለዋል።

"በአዲስ አበባ ያሉ ባለስልጣናት ይህንን ያውቃሉ። እናንተም ታውቃላች። እገዳው አሁንም እንደቀጠለ ነው" ብለዋል።

የሰራዊቱ መውጣት በጣም አስፈላጊ የሆነው የምግብ እርዳታ በረሃብ ለተጠቃችው ትግራይ ክልል እንደ ልብ ሊገባ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መግለፃቸውም በዚህ ዘገባ ሰፍሯል።

"ሰራዊታችን መላውን አፋር ለቆ ወጥቷል" በማለት አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ህወሃት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ሰራዊቴን አስወጥቻለሁ የሚለውን ዘገባ አስመልክቶ የፌደራሉ መንግሥትን ምላሽ ለማግኘት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽንን እንዲሁም የአፋር ባለስልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካችን ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል።

ነገር ግን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት 74 እርዳታ የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መኪኖች ወደ ትግራይ እየሄዱ ነው በሚል ከሶስት ቀናት በፊት ባሰፈረው የሚያዝያ 15 መግለጫው የትግራይ ኃይሎች ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል።

በዚሁ መግለጫ ላይ በተጨማሪም ወደ ትግራይ የሄዱና ያልተመለሱ 1025 የጭነት መኪኖች እንዲመለሱና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግም ጠይቋል።

ከቀናት በፊት ህወሃት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለመውጣት ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ አሰራር መዘርጋትና የተቋረጡ መሰረተ ልማት አገልግሎቶች መመለስን ጨምሮ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል።

በወቅቱም እንደ ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀመጡት መካከል ለትግራይ ህዝብ ወሳኝ የሆነው ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ አስተማማኝ መተላለፊያዎች (ኮሪደሮች) መኖር፣ ዘላቂ፣ ያልተገደበ፣ ወቅታዊ እና በቂ የሆነ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንዲሁም በትግራይ የተጣለው እገዳ ተነስቶ አስፈላጊው የማህበራዊ ኢኮኖሚ አገልግሎት መመለስ እንዳለበት የህወሃት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረው ነበር።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች ተቋርጠው ይገኛሉ።

ሮይተርስ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አህመድ ሃሪፍን ያናገረ ሲሆን እሳቸውም የትግራይ ሃይሎች ከአብዓላ ከተማ ለቀው ቢወጡም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባሉ ሶስት ወረዳዎች ይገኛሉ ብለዋል።

አብዓላንና እና መቀለን የሚያገናነኘውን አውራ መንገድንም የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረው እንዳሉ ኮሚሽነሩ መናገራቸውን ጭምር ያስነበበው ዘገባው መረጃዎችን ከአካባቢው ባለስልጣናትና ሚሊሻዎችም እያገኙም እንደሆነ መናገራቸውም ሰፍሯል።

የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ ወረዳዎችን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ነበር።

ከዚህ ቀደም የአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ኻሎይታ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን ተናግረው ነበር።

በኪልበቲ ረሱ ዞን በህወሓት ቁጥጥር ሥር ገብተዋል ተብለው ከነበሩት 5 ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲ እና በራህሌ ይገኙባቸዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ለማቆም ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል።

የትግራይ ኃይሎችም በቂ እርዳታ ወደ ክልሉ "በተመጣጣኝ ጊዜ" እስከደረሰ ድረስ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደሚያከብሩ መናገራቸው ይታወሳል።

መንግሥት ግጭት የማቆም ውሳኔውን ባስታወቀበት መግለጫው የትግራይ ኃይሎች ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ጠይቆ ነበር።

ከሰሞኑ ህወሃት ሰራዊቱን ኢሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው የአፋር ክልል አስወጥቻለሁ ያለ ሲሆን ከዚህም ውሳኔ ላይ የደረሰው ለሰብአዊነት ሲባል የተደረሰው ስምምነት ተከብሮ ያልተገደብ ሰብአዊ እርዳታ ትግራይ እንዲደርስ ነው ማለቱ ይታወሳል።

የተኩስ አቁሙ ከታወጀ በኋላ የትናንትናውን ጨምሮ የደረሰው 144 የእርዳታ መኪኖች መሆናቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም መረጃም የሚጠቁም ሲሆን እርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መድረስ አልተቻለም ተብሏል።

በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ እርዳታ ተቋርጦ ስለቆየ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን ቦስስት እጥፍ አድጎ፣ 300 መኪኖች በቀን እንዲገባ ከተራድኦ ድርጅቶቹ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ከሰሞኑ ገልጿል።

በክልሉ 400 ሺህ ህዝብ የሚሆን በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም አስቸኳይ የምግብ እና መድኃኒት እርዳታም ይሻሉ ተብሏል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።

አስራ ስምንት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።