ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሳተላይ ምስሎች ታጣቂዎች ዶግ አመድ ያደረጓትን የኦሮሚያ አንስተኛ ከተማ አሳዩ
ሰኞ ጥር 16/2014 ያጋጠመው ክስተት የአንዲት መንደር ነዋሪ አርሶ አደሮችን ሕይወት እስከ ወዲያኛው የቀየረ ክስተት ነበር።
በዕለቱ በምዕራብ ኦሮሚያ በምትገኘው እና ፊጤ በቆ ወደ ምትሰኘው መንደር ታጣቂዎች ዘልቀው ገብተው፤ ተኩስ ከፈቱ፤ መኖሪያ ቤቶች ላይ እሳት ለኮሱ፣ የሰው ሕይወት ቀጠፉ።
ከጥቃቱ ያመለጡ የመንደሯ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ብለው ቀያቸውን ጥለው ተሰደዱ። ይህ ዘገባ እስከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የፊጤ በቆ ነዋሪዎች ወደ መንደሯ አልተመለሱም።
ፊጤ በቆ የምትገኘው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ገሊላ ወረዳ ውስጥ ነው።
ቢቢሲ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም፣ በአካባቢው የተነሱ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመመርመር እንዲሁም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ እና ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎችን በማነጋገር በመንደሯ የተፈጠረው ምን እንደሆነ ማረጋገጥ ችሏል።
በተለያዩ የወለጋ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ መኖሪያ ቤት እና እህል የማቃጠል ተግባራት ሶስት ቡድኖችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር (መንግሥት ሸኔ) የሚለው ቡድን፣ የአማራ ታጣቂዎችን እንዲሁም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ናቸው በነዋሪዎች በጥፋት የሚወነጀሉት።
በፊጤ በቆቲ የሆነው ምን ነበር?
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ የ54 ዓመት ጎልማሳ ተወልደው ካደጉባት መንደር ተፈናቅለው ከስምንት የቤተሰብ አባላታቸው ጋር ተደብቀው ይገኛሉ።
"ከባድ መሳሪያዎች የታጠቁ ናቸው። የግንቦት 7 የሚባለውን ባንዲራ ነው የሚይዙት። ዱላ ይይዛሉ እንዲሁም ባንዲራውን ግንባራቸው ላይ አስረው ነው የሚንቀሳቀሱት።"
በመንደሯ የሆነውን አይቻለሁ የሚሉት እኚህ ጎልማሳ "የአማራ ታጣቂዎች ናቸው" የሚሏቸው ቡድኖች በመንደሯ ላይ ሰኞ ጥር 16/2014 አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የጀመሩት ጥቃት እስከ ምሽት 3 ሰዓት መዝለቁን ያስረዳሉ።
"እስከ ሶስት ሰዓት ድረስ እዛው ነበሩ። ሲዘፍኑ ነበር። የሚያቃጥሉትን አቃጥለው የሚወስዱትን ወስደው [ሄዱ] . . . የተመቻቸውን ነው የወሰዱት፤ የቀረውን ደግሞ በመጥረቢያ ነው የፈለጡት።" በማለት የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።
እኚህ ጎልማሳ መኖሪያ ቤታቸው መቃጠሉን እና በገንዘብ "ይህ ነው" ብለው መገመት ያልቻሉት ንብረት እንደወደመባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከሶስት ሄክታር መሬት ተሰብስቦ የነበረው በቆሎ እዛው ተቃጥሏል። ሞተር ወስደውብኛል። ቤቴ ከነ ሙሉ ንብረቱ ተቃጥሏል። ሕይወታችን ብቻ ነው የተረፈው. . . ።" ይላሉ
የሳተላይት ምስሎች ምን ያሳያሉ?
በቅርቡ የከተማ አስተዳደር ደረጃን ያገኘችው ፊጤ በቆ፤ በእርሻ ስራዎች ትታወቃለች። የፊጤ በቆ አፈር በቆሎ፣ ቦሎቄ እና ለውዝ በስፋት ያበቅላል።
ይህ ጥቃት የተሰነዘረው ደግሞ እህል ከማሳ ተሰብሰቦ በተከመረበት ወቅት ነው።
"በቆሎ ከአገዳው ላይ ሳይሰበር፤ የአምስት ኢንቬስተሮች እርሻ ተቃጥሏል። እያንዳንዳቸው 300 እና 400 ሄክታር እርሻ ሙሉ በሙሉ ነው የተቃጠለባቸው" ይላሉ።
ቢቢሲ ከፕላኔት ላብስ ያገኛቸው የሳተላይት ምስሎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው። ከድርጅቱ የተገኙት ሦስት ምስሎች ፊጤ በቆ ጥር 8፣ 17 እና 20 2014 ዓ.ም. የነበረችበትን ሁኔታ ጥርት ባለ ሁኔታ አሳይተዋል።
ከዚህ በታች ያለው የሳተለይት ምስል የተነሳው ጥር 8/2014 ዓ.ም. ነው። በእለቱ ምንም የደረሰ ቃጠሎ አለመኖሩን ከምስሉ መረዳት ይቻላል።
ከዚህ ቀጥሎ የተገኘው የሳተላይት ምስል ጥር 17/2014 ዓ.ም. የተነሳ ነው።
ጥር 17 የተወሰደው የሳተላይት ምስል ፊጤ በቆ ከተማ እና ዙሪያው በእሳት ዶግ አመድ መሆናቸውን ያሳያል። ይህም የዓይን እማኞች ከተማዋ ሰኞ ጥር 16/2014 በታጣቂዎች መውደሟን ከሰጡት የእማኝነት ቃልን ትክክለኛነት ያረጋግጣል።
ምስሉ ከተማዋ እና ዙሪያዋ ጠቁረው፤ ጥቁር ጭስ ከአካባቢው ሲወጣ ያሳያል።
የፊጤ በቆ ከተማ እና ዙሪያዋ የደረሰባቸውን ከፍተኛ ውድመት የሚያሳየው ጥር 20/2014 ዓ.ም. የተወሰደው የሳተላይት ምስል ነው።
ይህ ምስል መኖሪያ ቤቶች እና የእርሻ ስፍራዎች ተቃጥለው ያሳያል።
ከሳተላይት ምስሎች በተጨማሪ ቢቢሲ የተላኩለትን ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች በመመርመር በዚህች የገጠር ከተማ ላይ የደረሰውን ጉዳይ ማጣራት ችሏል።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ፎቶ ግራፎችን ላይ የሚታዩትን የመሬት አቀማመጦች ከጉግል ኧርዝ ጋር በማዋደድ የተቃጠሉት መኖሪያ ቤቶች መገኛቸው ፊጤ በቆ ከተማ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
ከዚህ በታች ባለው የመጀመሪያው ምስል ላይ የተያያዙት ሁለቱ ምስሎች ተመሳሳይ መሆናቸውን በአቀማመጣቸው መሠረት በጉጉል ኧርዝ ማረጋገጥ ይቻላል። አንድ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ሊሆኑ የሚችሉትን በተመሳሳይ ቀለም ተከበዋል።
ከላይ ያለው ከተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የተወሰደ ሲሆን ከስር ያለው ደግሞ ከጉግል ኧርዝ የተገኘ ምስል ነው።
ይህም ብቻ አይደለም፤ በስፍራው የደረሰውን ውድመት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ትክከለኛነት ከክስተቱ በኋላ ከተወሰደ የሳተላይት ምስል ጋር ማመሳከር ችለናል።
ከዚህ በታች በምስሉ የሚታዩት የወደሙት መኖሪያ ቤቶች፣ ወደ ግራ የምትታጠፈው ቀጭኗ መንገድ እንዲሁም የገጠር ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈው ሰፊው መንገድ ከሳተላይት ምስሎች ጋር ይጣጣማል።
ታጣቂዎቹ ፍላጎታቸው ምንድን ነው?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂዎች የአካባቢው ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋሉ።
"'ይሄ የእኛ አገር ነው። ይህን በረሃ ተዉልን። ከጉትን ጀምሮ እስከ ኡኬ እና ጊዳ ያለው የአማራ ነው' ይሉናል" ይላሉ ስማቸውን አንጠቅስም ያልናቸው የ54 ዓመቱ ጎልማሳ።
እኚህ ጎልማሳ ታጣቂዎቹ በአማራ ክልል ውስጥ ልዩ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እንዳለው ሁሉ በኦሮሚያ ክልልም "ልዩ የአማራ ዞን" እንዲኖር ይፈልጋሉ ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ታጣቂዎቹ ጥቃት የሚያደርሱብን እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።
"'ሸኔ በተደጋጋሚ ችግር እያደረሰብን ነው። እሱን እንፈልጋለን። . . . የምታኖሯቸው እናንተ ናችሁ' ይሉናል" ይላሉ ለቢቢሲ ቃላቸው የሰጡት ጎልማሳ።
በምዕራብ ሸዋ እና በአራቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ቡድን በአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲያደርስ ቆይቷል።
መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀው ቡድን በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ ከፈጸመ በኋላ አማራ ናቸው የሚባሉ ታጣቂዎች በበቀል በሚወስዱት እርምጃ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች እንደሚገደሉ እና ንብረታቸው እንደሚወድም ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።
የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት 'የአማራ ጽንፈኞች' ብለው የሚጠሩትን ቡድን አደረጃጀት እና አመራር በትክክል ማወቅ ስላልተቻለ በጉዳዩ ላይ የዚህን ቡድን አስተያየት ማካተት አልቻለንም።
የፊጤ በቆ ነዋሪዎች አሁን በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?
ይህ ጥቃት ጥር 2014 ዓ.ም. ከተፈጸመ በኋላ የገጠር ከተማዋ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው አልተመለሱም።
ተፈናቅለው የሚገኙት ነዋሪዎች እስካሁን ያገኘነው አንዳችም ድጋፍ የለም ይላሉ።
"'ቤታችሁ የተቃጠለባችሁ ስማችሁን መዝግቡ' ብለውን ነበር። የአካባቢው አመራሮች ራሳቸው ሸሽተው ሌላ ቦታ ነው ያሉት። በስልክ ነው ስም ያስተላለፍነው። እስካሁን ድረስ አንዳችም ነገር ከመንግሥት የተደረገልን ድጋፍ የለም" በማለት የ54 ዓመቱ ጎልማሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።