በዩኬ ጥገኝነት የሚጠይቁ በነጠላ የአየር ቲኬት ወደ ሩዋንዳ ይሸኛሉ ተባለ

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ኢንግሊሽ ቻናል ተብሎ በሚጠራው የውሃ አካል በኩል ወደ ዩኬ የሚገቡ አብዛኛዎቹን ጥገኘነት ጠያቂዎች በነጠላ የአውሮፕላን ቲኬት ወደ ሩዋንዳ እሸኛለሁ አለ።

ይህ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ አስተዳደር ሕግ በደረቅ ጭነት መኪኖች ተደብቀው ዩኬ የሚገቡ ወንድ ጥገኘነት ጠያቂዎችንም ይመለከታል ተብሏል።

ቦሪስ ጆንስን ይህ የ120 ሚሊዮን ፓዎንድ ፖሊሲ፤ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ያድናል ብለዋል።

የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የዩኬ መንግሥት እቅድን አጥብቀው ተችተዋል። የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶቹ ይህ ፕሮግራም ዩኬን ሊያስወጣ ስለሚችለው ከፍተኛ ወጪ እና የሩዋንዳ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ጥያቄ ውስጥ ከትተዋል።

ቦሪስ ጆንሰን፤ "ሀዘኔታችን ልክ ላይኖረው ይችላል። ሰዎችን የመርዳት አቅማችን ግን የተገደበ ነው" ብለዋል።

"የትኛውም እዚህ መጥቶ ለመኖር ፍላጎት ያለውን ሰው ወጪ ለመሸፈን የብሪታኒያ ታክስ ከፋዮችን ገንዘብ ልንጠይቅ አንችልም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ተቃዋሚው የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪዬር ስታርመር ይህን የዩኬ መንግሥት እቅድ፤ "ሊተገበር የማይችል" እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮቪድ ክልከላዎችን ተላልፈው ተገኝተው የቀረበባቸውን ትችት ለማስቀየር ያመጡት ሃሳብ ነው ሲሉ ኮንነዋል።

እአአ 2021 ላይ አነስተኛ ጀልባዎችን በመጠቀም 28ሺህ 526 ሰዎች ወደ ዩኬ መግባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። "ትናንት [ረቡዕ ሚያዝያ 5/2014] 600 ሰዎች ተሻግረዋል። ይህ አሃዝ በሚቀጥሉት ሳምንታት በቀን 1ሺህ ይሆናል።" ብለዋል።

በቀጣይ ዓመታት አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የመቀበል አቅም አላት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሩዋንዳን በዓለማችን ካሉ ደኅንነቷ የተጠበቀች አገር ናት ሲሉ አሞካሽተዋታል።

የዩኬ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ለመፈራርም ኪጋሊ ይገኛሉ።

ሚኒስትሯ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ዩኬ የሚገቡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ ይዘዋወራሉ ብለዋል።

የስደተኞች ቅበላን በተመለከተ በዩኬ እና ሩዋንዳ መንግሥታት መካከል የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር እስካሁን ይፋ አልሆነም። ይሁን እንጂ ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ እንዲሸጋገሩ የሚደረጉት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ነጠላ ወንዶች እንደሚሆኑ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሠረት ሩዋንዳ ከዩኬ የምትቀበላቸውን ስደተኞች የጥገኘነት ጥያቄ ትመረምራለች።

የስደተኛው የጥገኘነት ጥያቄ ምላሸ የሚያገኝ ከሆነ በሩዋንዳ እንዲኖር ይፈቀድለታል። በሩዋንዳ የመኖር ፍላጎት የሌለው ስደተኛ ወደ ትውልድ አገሩ ወይም ሊቀበለው ወደሚችለው ሦስተኛ አገር ሊዘዋወር ይችላል።

ቢቢሲ ወደ ሩዋንዳ የሚዘዋወር ስደተኛ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታን ተመልክቷል።

ሩዋንዳ በአሁኑ ወቅት በዓመት 500 ጥገኛ ጠያቂ ሰዎችን ሊያስተናግድ የሚችል 100 ማረፊያ ቦታን አዘጋጅታለች።

የሩዋንዳ መንግሥት ስደተኞች በአገሪቱ ሕግ ሙሉ ጥበቃ ይደረግላቸዋል ብሏል። "እኩል የሥራ ቅጥር መብት፣ የጤና እና የማሕበራዊ አገልግሎቶችን ያገኛሉ" ብሏል የኪጋሊ መንግሥት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንስን ይህ የአስተዳደራቸው መመሪያ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።

በእቅዱ መሠረት የሩዋንዳ መንግሥት ለሙከራ የሚውል የመጀመሪያ 120 ሚሊየን ፓውንድ ይሰጠዋል ተብሏል፤ ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች የሙሉ እቅድ አመታዊ ወጪው በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል።