ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢለን መስክ ትዊተርን የመግዛት ጥያቄ አቀረበ
ቢሊየነሩ የቴስላ አለቃ፣ ኢለን መስክ የትዊተርን "አስደናቂ አቅም" ማጉላት የምችለው እኔ ነኝ በሚል ማሕበራዊ ገጹን የመግዛት ጥያቄ አቀረበ።
መስክ የማሕበራዊ ሚዲያውን ጠቅላላ ዋጋ 41 ቢሊዮን የሚያደርስ በሼር 54.20 ዶላር ለመክፈል ጠይቋል።
በቅርቡ መስክ የትዊተርን ከፍተኛ ድርሻ መግዛቱ ይታወሳል። ኢላን መስክ የትዊተርን 9.2 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ መግዛቱን ተከትሎ በኒው ዮርክ የትዊተር አክሲዮን ሽያጭ 27 በመቶ አሻቅቦ ነበር።
መስክ ትዊተርን ለመግዛት ያቀረበው የግዢ ጥያቄ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ፤ "በተቋሙ ያለኝን ባለድርሻነት መልሼ ማጤን አለብኝ" ብሏል።
መስክ ባሳለፍነው የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ለትዊተር ቦርድ ማሕበራዊ ሚዲያውን የመግዛት ጥያቄ በጽሑፍ ወይም በድምጽ መልዕክት ጥያቄ ማቅረቡ ተገልጿል።
መስክ የትዊተር ቦርድ አባል እንዲሆን ተጠይቆ ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ትዊተር እሁድ ላይ አስታውቋል።
ኢለን ለትዊተር ቦርድ የላከው መልዕክት
"በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደተመላከተው፤ ይህ ኩባንያ በሚያስፈልገው ለውጥ ውስጥ እንዲያልፍ ወደ ግል ይዞታ መተላለፍ አለበት።
ባለፉት በርካታ ቀናት ብዙ ካሰብኩበት በኋላ፤ ኩባንያውን ለመግዛት እና የግል ለማድረግ ወስኛለሁ።
ዛሬ ምሽት ኩባንያውን የምገዛበትን ዋጋ አሳውቃችኋላሁ፤ ንጋት ላይ ደግሞ ይፋ ይሆናል።
በጉዳዩ ማውራት እንችላለን?
ከፍ ያለ ዋጋ ነው የምሰጠው፤ ባለደርሻዎች ደስተኛ ይሆናሉ።
የግዢ ስምምነቱ የማይሳካ ከሆነ፤ በአስተዳደሩ ላይ እምነት ስለሌለኝ፤ በተቋሙ ውስጥ ያለኝን ባለድርሻነት መልሼ ማጤን አለብኝ።
ይሄ ማስፈራራት አይደለም። አስፈላጊ ማስተካከያዎች ሳይደረጉ ኢንቨስት ማድረግ ትክክል አይሆንም።
እነዚህ ለውጦች ተቋሙ ወደ የግል ይዞታ ሳይሸጋገር ሊፈጸሙ አይችሉም"