ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
20 ዓመት ጓንታናሞ የታሠረው አልጄሪያዊ ወደ ሃገሩ ተላከ
ለ20 ዓመታት ገደማ ጓንታናሞ ቤይ በተሰኘው ጥበቃው የከፋ እሥር ቤት የከረመው አልጄሪያዊ ወደ ሃገሩ መመለሱን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገልጠዋል።
ሱፊያን ቡርሃሚ በፈረንጆቹ 2002 ፓኪስታን ውስጥ ከአንድ ነባር የአል-ቃዒዳ አባል ጋር ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።
አሜሪካ ውስጥ የቦምብ ጥቃት ለማድረስ አቅደሃል ብላ ነው አሜሪካ ሱፊያንን ዘብጥያ የጣለችው።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ግለሰቡን ከዚህ በላይ ማሠር ጠቀሜታ የለውም ብዬ ለቅቄዋለሁ ብሏል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አልጄሪያ ሱፊያንን ስብዕና በተመላበት መንገድ እንከባከበዋለሁ ስትል ቃል ገብታለች ይላል።
ሚኒስቴሩ በለቀቀው መግለጫ ሱፊያን የተለቀቀው ባለሥልጣናቱ "የደኅንነት ሁኔታው ማረጋገጫ ከተሰጠን" እንልቀቀው በማለታቸው ነው ብሏል።
"አሜሪካ የአልጄሪያን ፈቃደኝነት ታመሰግናለች" ሲል መግለጫው ያትታል።
መግለጫው አክሎ "ሌሎችም ጓንታናሞ ቤይ እንዲዘጋና በቁጥጥር ሥር ያሉ ግለሰቦች ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲተላለፉ እገዛ ለሚያደርጉ እናመሰግናለን" ይላል።
ሚኒስቴሩ ስለ ሱፊያን ከዚህ የዘለለ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
አልጄሪያ እስካሁን ስለሱፊያን ቡርሃሚ ጉዳይ ኦፊሴላዊ አስተያየት አልሰጠችም።
አሁን ጓንታናሞ ቤይ በተሰኘው በጭካኔያዊ አገዛዙ በሚታወቀው እሥር ቤት 37 ያለፍርድ የታሠሩ ሰዎች አሉ።
ጓንታናሞ ቤይ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የደቡብ ምስራቅ ኩባ መቀመጫ ነው።
ከ2002 ጀምሮ ይህ ሥፍራ አሜሪካ "ሽብር ላይ በማደርገው ጦርነት ሳቢያ በቁጥጥር ሥር የዋሉ" የምትላቸውን ግለሰቦች የምታቆይበት ነው።
በተለይ ደግሞ 9/11 ተብሎ ከሚታወቀው የሽብር ጥቃት በኋላ በርካታ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ወደዚህ ቦታ ተግዘዋል።
የአሜሪካ ደኅንነት ሰዎች ጓንታናሞ ቤይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ አሰቃይተዋል ተብለው ይወቀሳሉ።