ዊል ስሚዝ በጥፊ ከተማታ በኋላ ከአዳራሹ ለመውጣት ፈቃደኛ አልነበረም- የኦስካር አካዳሚ

ዊል ስሚዝ ክሪስ ሮክን በጥፊ ከመታ በኋላ ከኦስካር ሽልማት ዝግጅት እንዲወጣ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልነበረም ሲል የኦስካር አካዳሚ ተናገረ።

የኦስካር አካዳሚ በተጨማሪ በዊል ስሚዝ ላይ "የስነ ስርዓት መጣስ"ምርመራም እንደጀመረም ተናግሯል።

ዊል ስሚዝ አሎፔሺያ በሚባል የጸጉር መነቃቀል እክል ምክንያት ጸጉሯ በረገፈው በባለቤቱ ጃዳ ፒንኬት ላይ የቀለደውን ክሪስ ሮክን መድረክ ድረስ በመውጣት መቶታል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመጀመሪያውን ኦስካር ያሸነፈው ተዋናዩ ከዝግጅቱ በኋላ ይቅርታ ጠይቋል።

አካዳሚው ባወጣው መግለጫው "ስሚዝ ዝግጁን አቋርጦ እንዲወጣ ተጠይቆ ፈቃደኛ አልሆነም። [ነገር ግን] እኛም ሁኔታውን በተለየ መንገድ ማስተናገድ እንችል እንደነበር እንገነዘባለን" ብሏል።

"የአካዳሚውን የስነምግባር መመሪያዎች በመጣሱም ስሚዝ ላይ የስነ ስርዓት ጥሰት ምርመራ መጀመሩን" አክሎ አስታውቋል።

እነዚህም ተገቢ ያልሆነ አካላዊ ንክኪ፣ ስድብ ወይም አስጊ ባህሪ እና የአካዳሚውን ታማኝነት መጣስን ያካትታሉ ብሏል።

አካዳሚው ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሚያካሂደው የቦርድ ስብሰባ ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስታውቋል። ይህም "ማገድ፣ ማባረር ወይም ሌሎች ማዕቀቦችን ሊያካትት ይችላል" ሲል መግለጫው ገልጿል።

ዊል ስሚዝ ከክሪስ ሮክ በተጨማሪ ዕጩዎችን፣ እንግዶችን እና ተመልካቾችን ይቅርታ ጠይቋል።

ክሪስ ሮክ ከዝግጅቱ በኋላ በሰጠው የመጀመሪያ አስተያየት ስለክስተቱ "አሁንም እያሰላሰልኩ ነው" ብሏል።

ቦስተን በተካሄደ የቀልድ ዝግጅት ትርኢት ላይ "የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት እንዴት አለፉ?" ሲል ህዝቡን በቀልድ መልክ ጠይቋል። ስለጉዳዩ ግን በስፋት ለመናገር እንዳልተዘጋጀ አስታውቋል።

ክሪስ ሮክ ለተሰበሰበው ህዝብ "የሆነውን ነገር እያሰላሰልኩ ነው። ስለዚህ በጉዳዩ ዙሪያ ወደፊት አስተያየት እሰጣለሁ። ቁም ነገር ይሆናል። አስቂኝም ሊሆን ይችላል። አሁን ግን አንዳንድ ቀልዶችን እነግራችኋለሁ" ብሏል።

የእሑድ ምሽቱ ክስተት ኮሜዲያኑ ክሪስ ሮክ በምርጥ ዘጋቢ ፊልም ዘርፍ ሽልማት ለመስጠት መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ የተከሰተ ነው። በኋላም ዊል ስሚዝ በምርጥ ተዋናይነት ዘርፍ የኦስካር አሸናፊ በመሆን ሽልማቱን ተቀብሏል።

ክሪስ ሮክ ስለ ጄዳ ፒንኬት የተላጨ ጸጉር ቀልዷል። ቀልዱ የተነገረው እአአ በ1997 የወጣውንና ዴሚ ሙር ጸጉሯን ተላጭታ በመሪ ተዋናይነት የተጫወተችበትን ጂአይ ጄን የተሰኘውን ፊልም በመጥቀስ ነው።

ጄዳ ፒንኬት በቀልዱ ወቅት ፊቷ ላይ ብስጭት ይነበብበት ነበር። መጀመሪያ ሲስቅና ሲያጨበጭብ የነበረው ዊል ስሚዝ መድረኩ ላይ በፍጥነት ደርሷል።

ኮሜዲያኑ በክስተቱ የተደናገጠ ቢመስልም ለታዳሚያኑ "በቴሌቪዥን ታሪክ ውስጥ ይህ ታላቁ ምሽት ነው" ብሏል።

ዊል ባወጣው ይቅርታ ላይ ባህሪው "ተቀባይነት የሌለው እና ምክንያት ሊሰጠው የማይገባ" መሆኑን ጠቅሷል።

በመግለጫው "ክሪስ በይፋ ይቅርታ ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። ከስርዓት ውጪ ነበርኩ፣ ተሳስቻለሁ" ብሏል።