በኦስካር ሽልማት ላይ በጥፊ የተማታው ዊል ስሚዝ ክሪስ ሮክን ይቅርታ ጠየቀ

ዊል ስሚዝ በኦስካር ሽልማት ስነ ስርዓት ወቅት ክሪስ ሮክን በጥፊ በመማታቱ ይቅርታ ጠየቀ። ባህሪውንም "ተቀባይነት የሌለው" ሲል ገልጾታል።

"ክሪስ በይፋ ይቅርታ ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። ስርዓት ሊኖረኝ ይገባ ነበር። ተሳስቻለሁ" ብሏል ስሚዝ በመግለጫው።

በክስተቱ ምክንያት የኦስካር ፊልም አካዳሚ ስሚዝን ካወገዘ እና ጉዳዩን እንደሚከታተል ካሳወቀ በኋላ ነው የይቅረታ የጠየቀው።

ኮሜዲያኑ ስለ ባለቤቱ ጃዳ ፒንኬት ስሚዝ በመቀለዱ ነበር ተዋናዩ ወደ መድረክ ወጥቶ ጥፊ ያቀመሰው።

ሮክ አልፖሲያ በተባለ ጸጉር በሚያረግፍ ህመም ምክንያት ጸጉሯን በተላጨችው ፒንኬት ስሚዝ መላጣ ላይ ነበር የቀለደው።

ከአፍታ ቆይታ በኋላ ዊል ስሚዝ የሜዳ ቴኒስ ጀግኖቹን ቬኑስ እና ሴሬና ዊሊያምስን አባት ሆኖ በተጫወተበት በኪንግ ሪቻርድ ፊልሙ የመጀመሪያውን ኦስካር ሽልማት አሸንፏል።

ስሚዝ በኢንስታግራም ገጹ ላይ በተለጠፈው መግለጫ "በየትኛውም መልኩ የሚፈጸም ብጥብጥ መርዛማ እና አጥፊ ነው" ብሏል።

"በሽልማቱ ስነ ስርዓት ላይ ያሳሁት ባህሪ ተቀባይነት የሌለው እና ምክንያት የለሽ ነበር። በእኔ ላይ የሚደረጉ ቀልዶች የሥራው አካል ናቸው። በጄዳ የጤና ሁኔታ ላይ መቀለዱን መሸከም ስላልቻልኩ በስሜታዊነት ምላሽ ሰጥቻለሁ።"

ስሚዝ "ከመስመር መውጣቱን" በመግለጽ በቀጥታ ሮክን ይቅርታ ጠየቋል። ለአካዳሚውን እና ለዊሊያምስ ቤተሰብንም ይቅርታውን አድርሷል።

"በባህሪዬ ምክንያት ለሁላችንም አስደሳች የነበረውን ምሽት ስላበላሸሁ በጣም አዝኛለሁ" ሲል ጽፏል።

ከስሚዝ ይቅርታ በፊት ከኦስካር ጀርባ ያለው ድርጅት "የስሚዝን ድርጊት አወግዛለሁ" ሲል በመግለጫው አሳውቋል።

"በክስተቱ ዙሪያ መደበኛ ምርመራ በይፋ ጀምረናል። በመተዳደሪያ ደንባችን፣ በስነምግባር መርሆች እና በካሊፎርኒያ ሕግ መሠረት ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንመረምራለን" ብሏል።

ሮክ በክስተቱ ዙሪያ ሃሳቡን ካልገለጸ ጉዳዩ የሚያበቃ አይመስልም። ኮሜዲያኑ ጉዳዩን ወደ ፖሊስ አለመውሰዱ ተገልጿል።

እንዲያውም ከመድረክ ጀርባ "የመሐመድ አሊ ቦክስ አርፎብህ ያለምንም ጭረት የምታመልጥበት ብቸኛው አጋጣሚ" ሲል ስሚዝ ታዋቂውን ቦክሰኛ ሆኖ መሥራቱን በማስታወስ ሳቅ ለመፍጠር መሞከሩ ተነግሯል።

የሮክ ቀልድ እአአ በ1997 የወጣውን ጂአይ ጄንን ፊልም የተንተራሰ ነው። ዴሚ ሙር ጸጉሯን ተላጭታ በመሪ ተዋናይነት ተጫውታለች።

ፒንክኬት ስሚዝ በቀልዱ ወቀት ዓይኖቿን በንዴት ስታዘዋውር ታይታለች። መጀመሪያ ሲስቅና ሲያጨበጭብ የነበረው ስሚዝ በፍጥነት መድረኩ ላይ በፍጥነት ደርሷል።

ኮሜዲያኑ በክስተቱ የተደናገጠ ቢመስልም ለታዳሚያኑ "ይህ በቴሌቪዥን ታሪክ ውስጥ ታላቁ ምሽት ነው" ብሏል።

ሮክ ከዝግጅቱ በኋላ "ለመክሰስ ፈቃደኛ አልሆነም" ሲል የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ለቫራይቲ አስታውቋል።

ጥፊውን የቀመሰው ሮክ መድረክ ላይ ለመገኘት ምክንያት የሆነውን የምርጥ ዘጋቢ ፊልም ሽልማት ሰጥቶ ወርዷል።

ስለ ጉዳዩም ገና በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

ከደቂቃዎች በኋላ በኪንግ ሪቻርድ የምርጥ ተዋናይ ሽልማትን ያነሳው ስሚዝ በሰጠው አስተያየት ሪቻርድ ዊልያምስ "የቤተሰቡ ተከላካይ" እንደሆነ እና እሱም በህይወቱ "ሰዎችን እንዲወድ እና እንዲጠብቅ" ጥሪ እንደተደረገለት ተናግሯል።

"ጥበብ ከህይወት ትቀዳለች። ስለ ሪቻርድ ዊሊያምስ እንደሚናገሩት እኔም እብድ አባት ነኝ። ፍቅር ደግሞ ብዙ የእብድ ነገር እንድትሠራ ያደርግሃል።"

አካዳሚው በድጋሚ እንደሚጋብዘው ተስፋውን ገልጾ ሃሳቡን ቋጭቷል።