ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኦስካር ሽልማት፡ ዊል ስሚዝ በታላቁ የሽልማት መድረክ ላይ ክሪስ ሮክን በጥፊ ተማታ
ተዋናይ ዊል ስሚዝ ኦስካርስ በተሰኘው የፊልም ጥበብ የሽልማት መድረክ የሚስቱን ስም አንስቶ ያብጠለጠለውን ታዋቂውን ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን በጥፊ ተማታ።
ክሪስ ሮክ፤ የዊል ስሚዝ ሚስት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝን የፀጉር ቁርጥ በቀልድ ወረፍ ካደረገ በኋላ ነው ይህ የተከሰተው።
ዊል ስሚዝ ከመቀመጫው በመነሳት ወደ መድረኩ አቅንቶ ክሪስ ሮክን በጥፊ አጋጭቶ ሲመለስ ብዙዎች ጉዳዩ ቀልድ ነው ብለው አስበው ነበር።
ነገር ግን ወደ ወንበሩ ከተመለሰ በኋላ "የሚስቴን ስም በ. . . አፍህ አታንሳ" ብሎ ሲጮህ ነው ብዙዎች ተዋናዩ ማምረሩን የተረዱት።
ስሚዝ ከዚህ ብዙዎችን ካስበረገገ ድርጊት በኋላ የኦስካር ሽልማቱን ሲያነሳ ለድርጊቴ ይቅርታ በሉኝ ብሏል።
"አካዳሚውን [ኦስካር ሸላሚው ኮሚቴ] እንዲሁም ለሽልማት የታጩ የተውኔት አጋሮቼን ይቅርታ መጠየቅ እሻለሁ" ሲል ተማፅኗል።
ዊል ስሚዝ፤ ኪንግ ሪቻርድ በተሰኘው ፊልም ላይ የቴኒስ ከዋክብቱን ቬነስና ሰሪና ዊሊያምስ አባት ሆኖ በመተወኑ ነው በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለስም የከበደውን የኦስካር ሽልማት ያገኘው።
"ጥበብ የሕይወት ቅጂ ናት። ልክ እንደ ተወንኩት ሪቻርል ዊሊያምስ የእብደት ሥራ ሠርቻለሁ። ነገር ግን ፍቅር የእብድ ሥራ እንድትሠሩ ያደርጋችኋል።"
ባለቤቱ ፒንኬት ስሚዝ ከዚህ በፊት የፀጉር መነቀል የሚያስከትል 'አላፒሺያ' የተሰኘ በሽታ እንዳለባት ተናግራ ነበር።
የዊል ስሚዝ ጥፊ ሰላባ የሆነው ክሪስ ሮክ በሁኔታው እጅግ ተደናግጦ "በቴሌቪዥን ታሪክ እጅግ አስደናቂውን ክስተት ታድመናል" ሲል ተደምጧል።
ክሪስ ሮክ ወደ መድረክ የወጣው በምርጥ የዘገባ ፊልም ዘርፍ አሸናፊ ለሆነው ግለሰብ ሽልማት ለመስጠት ነበር።
ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ዶልቢ ቲያትር በተባለው ግዙፍ መድረክ ላይ ዊል ስሚዝ የፈፀመው ድርጊት ብዙዎችን አጀብ አሰኝቷል።
ብዙዎች ዊል ስሚዝ የሙያ አጋሩን በጥፊ ያጋጨው እየቀለደ እንዳልሆነ የገባቸው ወደ መቀመጫው ተመልሶ አፀያፊ ቃል ከተጠቀመ በኋላ ነው።
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን በቴሌቪዥን ሲያሰራጭ የነበረው ኤቢሲ የተሰኘው ጣቢያ ይህን የዊል ስሚዝ ንግግር ከማስተላለፍ ተቆጥቧል።
ፒንኬት ስሚዝ ፌስቡክ ላይ በምታሰራጨው ሬድ ቴብል ቶክ በተሰኘው ዝግጅት ላይ ፀጉር የሚያሳጣ በሽታ እንዳለባት ይፋ ያደረገችው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር።
"ለመጀመሪያ ጊዜ ፀጉሬን እየታጠብኩ ተነቅሎ ሲወድቅ በጣም ደንግጬ ነበር። ለዚህ ነው ብዙውን ጊዜ ፀጉሬን የምላጨው።"
ዊል ስሚዝ የባለቤቱ ስም ተነስቶ ሲብጠለጠል ሊዋጥለት ባለመቻሉ ከኦስካርስ ሽልማት ታሪክ የማይፋቅ ድርጊት ፈፅሟል።
ከዚህ ድርጊት ለጥቆ ደግሞ በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦስካር ሽልማት በማንሳት ሌላ ታሪክ ፅፏል።
ሽልማቱን ለመቀበል ወደ መድረኩ ድጋሚ ካቀና በኋላ የይቅርታ ቃሉን አሰምቶ ንግግር ሲያደርግ አምላኩን አመሰግኗል።
"በዚህ ቢዝነስ [የፊልም ዓለም] ውስጥ እስካለን ድረስ ሰዎች ስለኛ የማይሆን ነገር ሲያወሩ ሰምቶ እንዳልሰሙ ማለፍን መቀበል እንዳለብኝ አውቃለሁ። ሰዎች እኛን የሚያንቋሽሽ ነገር ሲያደርጉ ፈገግ ብለን ማለፍ እንዳለብን እረዳለሁ" ብላል ስሚዝ።
"መቼም በቀጣይ ዓመትም እንደምትጋብዙኝ ተስፋ አለኝ" በማለት ነው ዊል ስሚዝ ንግግሩን የቋጨው።