ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ስልታዊ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ጥቅም ላይ ታውል ይሆን?
ሩሲያ ዩክሬንን በወረረች በአጭር ጊዜ ውስጥ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ወሳኝ ኃይላቸውን" ማለትም የኒውክሌር መሳሪያዎችን እያንቀሳቀሱ መሆናቸውን በመግለጽ "ለውጊያ ዝግጁ" ሆነው በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ይህ ውሳኔ ምዕራባውያን ሩሲያ የምርም ስልታዊ (ታክቲካል) የኒውክሌር መሳሪያዎችን ትጠቀም ይሆን የሚል ግራ መጋባት ውስጥ ከቷቸዋል። ሩሲያ ምንም እንኳን የኒውክሌር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ትጠቀማለች ብሎ ማሰብ ቢከብድም የፕሬዝዳንት ፑቲን አካሄድ ግን አስፈሪ እየሆነ ነው።
ስልታዊ ኒውክሌር መሳሪያዎች ምንድናቸው?
ስልታዊ/ታክቲካል የኒውክሌር መሳሪያዎች ከዋናው የኒውክሌር መሳሪያዎች ጋር ሲነጻጸሩ በጣም አጭር ወደሆነ ርቀት የሚተኮሱ ናቸው። ይህ ደግሞ ስትራቴጂክ ከሚባሉት የኒውክሌር መሳሪያዎች በእጅጉ ይለያዋል።
በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ሁለቱ የወቅቱ ኃያላን አገራት አሜሪካ እና ሶቪየት ሕብረት አንዳቸው ወደ አንዳቸው እንደሚተኩሱት ሲዝቱት የነበረው ረጅም ርቀት ተጓዡ የኒወክሌር መሳሪያ ነው ስትራቴጂክ የሚባለው።
በሌላ በኩል ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ደግሞ አጭር ርቀት የሚጓዙና ትንንሽ ቦምቦችን እንዲሁም በጦርነት አውድማ ላይ በጥቅም ላይ የሚውሉ ሚሳኤሎችን ጭምር ያካትታል።
ሩሲያ ምን አይነት ታክቲካል የኒውክሌር መሳሪያዎች አሏት?
ሩሲያ እስከ 2000 የሚገመቱ ታክቲካ የኒውክሌር መሳሪያዎች እንዳሏት ይገመታል። እንዚህ መሳሪያዎች ታዲያ የታቀደላቸውን ኢላማ ለመምታት ማንኛውም አይነት ተተኳሽ አረር ሊሸከሙ የሚችሉ ናቸው።
ሌላው ቀርቶ በቅርብ ርቀት በሚደረጉ ውጊያዎች ጭምር እየተተኮሱ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ናቸው፤ ታክቲካል የኒውክሌር መሳሪያዎች።
እንዚህ መሳሪያዎች በጦር አውሮፕላኖች እንዲሁም መርከቦች ላይ ተጠምደው ሰርጓጅ መርከቦችን እና ተምዘግዛጊ የውጊያ መሳሪያዎችን ኢላማ ለማድረግም ጥቅም ይውላሉ።
ታዲያ እኚህ የጦር መሳሪያዎች በአሁኑ ጊዜ ለጦርነት ዝግጁ ሆነው መተኮስ የሚችሉ አይደሉም፤ በሆነ ምስጢራዊ ቦታ መጋዘን ውስጥ በጥንቃቄ ተቀምጠው የሚኙ ናቸው።
ነገር ግን ሩሲያ ስትራቴጂክ ሚሳኤሎችን ከመጠቀም ይልቅ እነዚህን የአጭር ርቀት ታክቲካል የኒውክሌር መሳሪያዎችን መጠቀም ልትመርጥ ትችላለች። ይሄ ደግሞ ጊዜ ሂደት የሚታይ ጉዳይ ነው።
"በኒውክሌር ላይ የተቀመጠውን ስምምነት በሚጥስ መልኩ ኒውክሌርን ላይጠቀሙት ይችላሉ፤ ነገር ግን ተራው ወታደር ጭምር ሊጠቀማቸው የሚችሉ ታክቲካል መሳሪያዎችን ግን ጥቅም ላይ ሊያውሉ ይችላሉ" ይላሉ በዓለም አቀፉ የደኅንነት ፕሮግራም ዋና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ፓትሪሺያ ሌዊስ።
ምን ያክል ጉዳት ያደርሳሉ?
ታክቲካል የኒወክሌር መሳሪያዎች በመጠንም ሆነ በአቅም በጣም የተለያየ አይነት አሰራር ነው ያላቸው።
ትንሹ የሚባለው ታክቲካል መሳሪያ አንድ ኪሎቶን ወይም አንድ ሺ ቶን የቲኤንቲ ፈንጂዎች አቅም በአንድ ላይ የያዘ ሲሆን ትልቁ ደግሞ እስከ 100 ኪሎቶን ድረስ ሊመዝን ይችላል። ይህ ቀላል ቁጥር አይደለም።
የሚያደርሱት ጉዳት ደግሞ እንደ ተሸካሚው የጦር መሳሪያ ፍጥነትና ግዝፈት እንዲሁም ከመሬት በምን ያህል ርቀት ነው የፈነዳው፣ የፈነዳበት አካባቢ ምን ይመስላል በሚሉ አንጻራዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
ነገር ግን በተግባራዊ መልኩ ለማወዳደር በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓን ሄሮሺማ ላይ የተጣለው ቦምብ 146 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን የገደለው የኒውክሌር መሳሪያ ክብደቱ 15 ኪሎቶን ብቻ ነበር።
አጠቃላይ ሩሲያ በእጇ ላይ ያሉ ታክቲካል የኒወክሌር መሳሪያዎች ደግሞ ቢያንስ 800 ኪሎቶን ይሆናሉ።
የፑቲን ስለኒውክሌር ደጋግሞ ማውራት አሳሳቢ ነው?
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ሩሲያ እነዚህን መሳሪያዎች ልትጠቀምባቸው እንደምትችል በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር። ምናልባትም በምዕራቡ ዓለም አገራት ዘንድ ትንሽ ፍራቻን ለመፍጠር ተደርጎም ተቆጥሮ ነበር።
የአሜሪካ ሰላዮች እንደሚሉት ፑቲን ይህንን አካሄድ የመረጡት ምዕራባውያን፣ በዩክሬን ላይ የተከፈተውን ወረራ ለማስቆም የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉና ውሳኔውን ለመቀልበስ እንዲየሳምኗቸው ነው እንጂ የምርም መሳሪያዎቹን የመጠቀም ፍላጎት ኖሯቸው አይደለም ይላሉ።
ነገር ግን ሌሎች ደግሞ ምንም እንኳን የመሆን ዕድሉ ጠባብ ቢሆንም ሩሲያ ግን በሆነ ምክንያት ተገፋፍታ እንዚህን ታክቲካል የኒውክሌር መሳሪያዎችን በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ስለመጠቀም ልታስብ ትችላለች።
የአሜሪካ የስለላ ተቋም እንደሚለው ሩሲያ 'ነገሮችን ለማብረድ ነገሮችን ማባበስ' የሚባል አስተሳሰብ ተከታይ ናት። ይህ ደግሞ የምርም ታክቲካል ኒውክሌር መሳሪያዎቹን ጦር ሜዳ ላይ በመጠቀም፣ የሆነ ቦታ ወታደራዊ ልምምድ ላይ ውጤታማነቱን በማሳየት፣ አልያም በቅርቡ የኒውክሌር መሳሪያዎችን ልጠቀም እችላለሁ እያሉ ማሰፈራራትን ያካትታል።
የዚህ አካሄድ ዋነኛ አላማው ሌሎችን በማስፈራራት ዞር እንዲሉ ማድረግ ነው።
በርካቶችን እያሳሰበ የሚገኘው ጉዳይ ቭላድሚር ፑቲን ምናልባት ያሰቡት ነገር ባይሳካላቸውና በዩክሬኑ ጦርነት እየተሸነፉ እንደሆነ ካሰቡ ታክቲካል ኒውክሌር መሳሪያዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የጦርነት አሰላለፉን ለመቀየር እንዲሁም አልተሸነፍኩም የሚለውን መልዕከት ለማስተላለፍ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ነገር ፑቲን እነዚህን መሳሪያዎች ለመጠቀም እንዲገደዱ በዩክሬን ያለው ሁኔታ አሁን ካለበት በእጅጉ መባባስ አለበት፣ አልያም በሩሲያ ከባድ ውስጣዊ ችግር መፈጠር አለበት።
"በጣም የምፈራው ነገር ፑቲን እዚህ ቦታ ላይ የሚደርሱ ከሆነ ዩክሬን ውስጥ የኒውክሌር መሳሪያ ጥቅም ላይ ሊያውሉ ይችላሉ። መንገዳቸው ላይ የሚመጡትን በሙሉ እያጠፉ ስለመሄድ ይሆናል ውሳኔው። አስካሁን ድረስ እዚህ ገፊ ቦታ ላይ ፑቲን አልደረሱም" ይላሉ በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ድርጅት ውስጥ ባለሙያ የሆኑት ጄምስ አክተን።
መሳሪያዎቹ ጥቅም ላይ ቢውሉ ለራሷ ሩሲያ ስጋት ይሆናሉ?
ፑቲን ዩክሬን የሩሲያ አካል እንደሆነች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። በዩክሬን ላይ መሳሪያዎችን ከተጠቀሙ ደግሞ እራስን በራስ እንደመውጋት ነው የሚቆጠረው።
"ሩሲያ ለዩክሬን በጣም ቅርብ ነች፤ የታክቲካ ኒውክሌር መሳሪያዎቹ ጉዳት እስከ ሩሲያ ድንበር ድረስ ሊደርስ ይችላል" ይላሉ ዶክተር ፓትሪሺያ ሌዊስ።
በዓለማችን ታሪክ የኒውክሌር መሳሪያዎች ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉት በሁለተኛ የዓለም ጦርነት መገባጃ አካባቢ አሜሪካ ጃፓን ላይ ቦምቦቹን ስትጥል ነበር።
ታዲያ ፑቲን መሳሪያዎቹን በመጠቀም ሁለተኛው መሪ ይሆኑ ይሆን? እዚህ ጋር ፑቲን ሌሎች አያደርጉትም ያሏቸውን ነገሮች በሙሉ አድርገው አሳይተዋል።
ፑቲን ክራይሚያን በጭራሽ አይነኩም ሲባል፣ ግዛቲቱን ከዩክሬን ነጥቀው በሩሲያ ቁጥጥር ስር አደረጉ። ዶንባስ ውስጥ ጦርነት አይጀምሩም ብለው በርካቶች ሲከራከሩ፤ ፑቲን ግን ጦርነቱን አስጀምረው በተግባር አሳዩ።
አሁን ዩክሬንንማ ዓይናችን እያየ አይነኩም ሲሉ ለነበሩ የምዕራቡ ዓለም አገራት፤ ፑቲን 'እስቲ ምን ትሆኑ' በሚመስል መልኩ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ አውጀዋል።
ይህ አካሄድ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ያመራ ይሆን?
እስካሁን ድረስ ማንም የታክቲካል ኒውክሌር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚለውን መገመት አይችልም። ነገሮች በጣም ተባብሰው እንኳን ፑቲን መሳሪያዎቹን ጥቅም ላይ ላለማዋል ሊወስኑም ይችላሉ።
ያደርጉታልም፣ አያደርጉትም የሚለውን ማወቅ እጅግ ፈታኝ ነው። ምን ሊፈጠር እንደሚችል አለማወቃችን ነው ስጋቱን ትክክለኛ የሚያደርገው።
አሜሪካ ጉዳዩን ከፍ ባለ ሁኔታ በትኩረት እየተከታተልኩት ነው ብላለች።
ሩሲያ ያሏትን የጦር መሳሪያዎች በሙሉ በተመለከተ አሜሪካ በአንድም ሆነ በሌላ ሁኔታ መረጃው አላት። ለምሳሌ ሩሲያ ታክቲካዊ መሳሪያዎቿን ለጦርነት ስታንቀሳቅስ አልያም በስትራቴጂክ ኒውክሌር መሳሪያዎች አካባቢ የተለየ እንቅስቃሴ ሲኖር በሰከንዶች ውስጥ መረጃው ይደርሳታል።
እስካሁንም ምንም አይነት አስጊ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት እየገለጹ ነው።
በሌላ በኩል ኔቶ ነገሮችን ስለማቀዝቀዝና ጉዳቶችን ስለመቀነስ ሊያስብ ይችላል። ሩሲያ ልታልፈው የማትችለው ቀይ መስመር ሊያስቀምጥ ይችላል። ሩሲያ ግን ምን ታደርጋለች የሚለው አይታወቅም።
"የኒውክሌር መሳሪያዎችን አንድ ጊዜ መጠቀም ከተጀመረ በእርግጠኝነት ማቆሚያ አይኖረውም። ማንም ሰው በትክክል ዓለማችን ምን ልትመስል ትችላለች የሚለውን ማወቅ አይችልም'' ይላሉ ጄምስ አክተን።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ሊያነቧቸው የሚገቡ ዘገባዎች፡