ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ እና ዩክሬን: ሩሲያ ጥቅም ላይ ልታውለው የምትችለው ምን ያክል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አላት?
ፕሬዝደንት ፑቲን የሩሲያን የኒውክሌር ኃይል በተጠንቀቅ እንዲቆይ ማዘዛቸው ዓለምን አስግቷል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች የፑቲን ማሳሰቢያ ምራባውያን በዩክሬን ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ለማድረግ የተላለፈ ቁጣ አዘል ማስጠንቀቂ እንጂ ንግግራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የመጠቀም ፍላጎት መኖሩን አያሳይም ይላሉ።
ሩሲያ ምን ያህል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አላት?
አገራት ያላቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ብዛት ግምታዊ ናቸው። እንደ አሜሪካ ሰይንቲስቶች ፌዴሬሽን ከሆነ ሩሲያ 5 ሺህ 977 የኒውክሌር አረሮች አሏት።
የኒውክሌር አረር የኒውክሌር ፍንዳታን ያስከትላል። ይህ አሃዝ ጊዜ አልፎባቸው ለመወገድ ዝግጁ የሆኑ 1 ሺህ 500 የሩሲያ የኒውክሌር አረሮችን ይጨምራል።
የተቀሩት ወደ 4 ሺህ 500 የሚጠጉት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች- ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ያጠቃልላል።
የተቀሩት አንስተኛ የሆኑ የሚያደርሱትም ጉዳት ዝቅ ያለ እና በውጊያ ወቅት በአጭር ርቀት የሚገኝን ዒላማ ለመምታት የሚተኮሱ ናቸው።
ይህ ማለት ግን ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ለተልዕኮ ዝግጁ የሆኑ የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ኒውክሌር መሳሪያዎች አሏት ማለት አይደለም።
ባለሙያዎች 1 ሺህ 500 የሚሆኑት አረሮች በሰርጓጅ መርከቦች ላይ እና በጦር ሰፈሮች ተጠምደው እንደሚገኙ ግምታቸውን ይሰጠሉ።
የሩሲያ የኒውክሌር አቅም ከሌሎች ሲነጻጸር
በዓለም ላይ ዘጠኝ አገራት የኒወክሌር ጦር መሳሪያ አላቸው።
እነሱም ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሕንድ፣ እስራኤል፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓኪስታን፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግድም ናቸው።
ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 191 አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለሌሎች አገራት አሳልፎ ያለመስጠት ስምምነትን ፈርመዋል።
በዚህ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት አገራት፤ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ክምችታቸውን ለመቀነስ እና በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የኒውክለር ጦር መሳሪያዎችን ለማስወገድ ተስማምተዋል።
ሕንድ፣ እስራኤ እና ፓኪስታን በዚህ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን አላኖሩም፤ ሰሜን ኮሩያ ደግሞ እአአ 2003 ላይ ከስምምነቱ እራሷን አግልላለች።
ከተጠቀሱት ዘጠን አገራት እስራኤል ብቻ ናት የኒውክሌር መሳሪያ እንዳላት በይፋ ያላመነችው፤ ይሁን እንጂ እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት እሙን ነው።
ዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የላትም፤ ፑቲን ግን ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ ዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ጥረት እያደረገች ነው ይላሉ።
የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ምን ያክል አውዳሚ ናቸው?
የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ከፍተኛ ውድመት እንዲያደርሱ ተደርገው ነው የተሰሩት።
ጦር መሳሪያዎቹ የሚያደርሱት የጉዳት መጠን በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረት ይሆናል። እነዚህም፤
- የአረሩ መጠን
- ፍንዳታው ከምድር በምን ያክል ከፍታ ላይ እንደሚከሰት እና
- ፍንዳታው የሚያጋጥምበት የአካባቢ ሁኔታ ናቸው።
ባለሙያዎች አነስተኛ የአረር መጠን ያለው የኒውክሌር ቢሆን እንኳ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ሊያደርስ እንደሚችል ይናገራሉ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓኗ ሂሮሺማ 146 ሺህ ሰዎችን የደገለው ቦምብ ክብደቱ 15 ኪሎቶን (15 ሚሊዮን ኪሎ ግራም) ይመዝን ነበር።
ዛሬ ላይ ያሉት የኒውክሌር አረሮች ከ1ሺህ ኪሎ ቶን በላይ ሊመዝኑ ይችላሉ።
የኒውክሌር ፍንዳታ ሲያጋጥም ከፍተኛ ኃይል ያለው ብርሃን ያወጣል። ፈንዳታው የሚፈጥረው የኃይል ንዝረት በርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኙ ሕንጻዎችን ጨምሮ በዙሪያው የሚያገኘውን ሁሉ እንዳልነበር ያደርጋል።
ከእአአ 1945 ወዲህ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በግጭት ወቅት ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም።
ሩሲያም የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን የምትጠቀመው በአራት አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ መሆኑን የአገሪቱ መመሪያ ያዛል።
- የሩሲያ ፌዴሬሽን አልያም አጋሮቿን ለማጥቃት ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ከተተኮሰ
- በሩሲያ ፌዴሬሽን አልያም በአጋሮቿ ላይ ኒውክሌር ጦር ወይም የጅምላ ፍጅት የሚያስከትል መሳሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ
- የሩሲያን የኒውክሌር ባለቤትነት የሚገዳደር በቁልፍ የመንግሥት ወይም የጦር ተቋማት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ እና
- የሩሲያ ህልውና አደጋ ላይ ወድቆ አገሪቱ በውጪ ኃይል ከተጠቃች ሩሲያ የኒውክሌር ኃይሏን ልትጠቀም ትችላለች።