ለአራት ወራት ታስረው ለቆዩት የአሶሺየትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ዋስትና ፈቀደ

አሚር አማን

የፎቶው ባለመብት, Amir/instagram

የምስሉ መግለጫ, አሚር አማን

ከወራት በፊት በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የቆዩት ሁለት የአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ጋዜጠኞች በዋስ እንዲለቀቁ ተወሰነላቸው።

የኤፒ ዜና ወኪል ጋዜጠኛው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አድርገዋል በሚል ነበር ተይዘው ለአራት ወራት በእስር ላይ የቆዩት።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የአሚር አማን ታናሽ ወንድም የሆነው ናድር አማን ለቢቢሲ እንደተናገረው አሚርን ለማስፈታት የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ለመክፈል ቤተሰቡ ጥረት እያደረገ ነው።

ነገር ግን ፖሊስ ይግባኝ ይጠይቃል የሚል ስጋት እንዳላቸው እና በእነርሱ በኩል ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይፈጸማል በሚል ተስፋ አስፈላጊውን ሂደት እየፈጸሙ መሆናቸውን ተናግሯል።

"መጀመሪያም መታሰር አልነበረባቸውም። ሥራቸውን ነው የሰሩት። ነገር ግን ላለፉት አራት ወራት ያህል ያለ ፍትህ ታስረው ቆይተዋል። አሁን በተሰጠው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቤተሰቡ ደስተኞች ነን። ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው'' ሲል ናድር የወንድሙ እስር በቤተሰቡ ላይ የፈጠረውን ጫና ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሁለቱን ጋዜጠኞች ከሌላ አንድ ግለሰብ ጋር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ኅዳር ወር አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ላይ ሲሆን መያዛቸው ይፋ የሆነው ከበርካታ ቀናት በኋላ ነበር።

በጋዜጠኞቹ ላይ በመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በቀረበው ዘገባ "ሽብርተኛ ቡድንን ለማስተዋወቅ ሲሰሩ ነበር" ሲል ፖሊስ ገልጾ ነበር።

የጋዜጠኞቹ አሰሪ የሆነው አሶሺየትድ ፕሬስ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ በመንግሥት የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረገው ሲሆን፣ "አሚር ኢላማ የሆነው የጋዜጠኝነት ሥራውን በማከናወኑ መሆኑ ግልጽ ነው" ብሏል።

"አሚር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግጭት ውስጥ ሁሉንም የሚመለከት ጠቃሚ ሥራዎችን ያከናወነ ነጻ ጋዜጠኛ ነው" ብሏል በመግለጫው ላይ።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ በነበረበት ወቅት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ አሚር እና ቶማስን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሆነው ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ ቆይተው ነበር።

ጋዜጠኞቹ ለተለያዩ ጊዜያት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ታስረው ከቆዩ በኋላ ብዙዎቹ በነጻ መለቀቃቸው ይታወሳል።

አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለሦስት ወራት ያህል በእስር ላይ ቆይተው ጉዳያቸው በተከታታይ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ነው ዛሬ በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነው።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ በመቀጠል ሁለተኛ ናት ማለቱ ይታወሳል።