በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መመለስ ተጀመረ

በቦሌ የደረሱ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

ኢትዮጵያ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎቿን ወደ አገራቸው የመመለስ ስራ በዛሬው እለት መጋቢት 21፣ 2014 ዓ.ም መጀመሯን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዛሬው ዕለት 498 የሚሆኑ ስደተኞች በቦሌ ዓለም አቀፍ ማረፊያ የደረሱ ሲሆን በባለስልጣናቱም አቀባበል መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

ስደተኞቹን ወደ አገራቸው ለመመለስና መልሶ ለሟቋቋም የተመሰረተው ብሔራዊ ኮሚቴ በሳዑዲ ያሉ ዜጎቹን የመመለሱን ተግባር በዛሬው ዕለት እንደሚጀምር ከሰሞኑ አስታውቋል።

አስራ ስድስት አባላት ያሉት ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ ሰኞ ዕለት ይህንን አስመልክቶ መምከሩም ተገልጿል።

ኮሚቴው ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከ7 እስከ 11 ባሉት ወራት ውስጥ ለመመለስ እንዳቀደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎ አስፍሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከዚህ ቀደም እንዳሉት በሰቆቃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለሱ ሂደት አለመቆሙንና የተወሰነ መቀዛቀዝ እንደነበር ጠቅሰው፣ ስደተኞችንም ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎቿን መመለስ ጀምራለች። የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት 498 ስደተኞችን ዛሬ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይም በገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመዴ ሽዴ የሚመራ የልዑክ ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ሁኔታ ላይ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ወደ ሪያድ አቅንቶ ከሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣንት ጋር ተወያይቶ ነበር።

በነዳጅ ምርት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰርቶ ለመቀየር መዳረሻ ከሚያደርጓቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ይሁን እንጂ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በተለያየ የወቅት በአገሪቱ የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም በሚል በርካታ ኢትዮጵያውያን እጅግ አስቸጋሪ በሆኑና በማያፈናፍኑ እስር ቤቶች እንደሚቆዩና ለበርካታ የጤና እክሎች መጋለጣቸውን ቢቢሲ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

እስረኞቹ በቂ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ በህይወት ለመቆየት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እንደሚያዙ ይናገራሉ።

በማቆያ ማዕከላትም ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ከመቆያታቸው ባሻገር በጥበቃዎች ማሰቃየትና ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጹ የሚታወስ ነው።

በዚህም የማዕከሉ ጥበቃዎች በጎማ በተሸፈነ ብረት በፈጸሙባቸው ድብደባ ስደተኞች መሞታቸውንም ተመልክቷል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሰቆቃ በሳኡዲ አረቢያ እስርእ ቤቶች