አብራሞቪች ዩክሬን ውስጥ የሰላም ድርድር ላይ ሳሉ ተመርዘው እንደነበር ተሰማ

ሮማን አብራሞቪች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያዊው ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪች ባለፈው ወር በዩክሬንና ቤላሩስ ድንበር አቅራቢያ በነበረው የሰላም ውይይት ላይ ተመርዘው እንደነበር ተሰማ።

የቱጃሩ የቅርብ ሰዎች ናቸው ይህን መረጃ ያሾለኩት።

የቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ባለቤት የሆኑት ሮማን አሁን ወደ ሙሉ ጤንነታቸው እንደተመለሱ ተገልጧል።

ሩሲያዊው ባለሃብት ከተመረዙ በኋላ ዓይናቸው ቀልቶ፤ ቆዳቸው ደግሞ እንደመላላጥ ብሎ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።

የሰላም ድርድሩም በዚህን ምክንያት እንደተስጓጓለ ተሰምቷል።

አንድ ዘገባ እንደጠቆመው ባለሃብቱ የተመረዙት የሰላም ድርድሩ እንዲስተጓጓል በፈለጉ ሩሲያዊያን ነው።

የሮማን አብራሞቪች መመረዝ ዜና ከወጣ በኋላ ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የሻቱ አሜሪካዊ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሰውዬው "ተመርዘው ሳይሆን የአየር መለዋወጥ አጋጥሟቸው ነው" ብሎ ፅፏል።

የዩክሬን ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ባለሥልጣን የሆኑት ኢሆር ዞቭካ ደግሞ ምንም እንኳ አብራሞቪችን ባያናግሯቸውም ድርድሩ ላይ የነበሩ ዩክሬናዊያን "ሰላም" መሆናቸውን አልፎም አንድ ግለሰብ የመመረዙ ዜና "ሃሰት ነው" ማለቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዓይን ሕመም

ልጥጡ ቱጃር እና ዩክሬናዊው እንደራሴ ሩስቴም ኡሜሮቭ በፈረንጆቹ መጋቢት 3 ካጋጠማቸው ክስተት እንዳገገሙ ዎል ስትሪት ጆርናል ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ለሩሲያዊው ቢሊየነር ቅርብ የሆኑ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግለሰቡ ከሕመማቸው አገግመው አሁንም የሰላም ድርድሩን ለማስቀጠል ጥረት እያደረጉ ነው።

ምንም እንኳ አብራሞቪች በሰላም ድርድር ላይ ያላቸው ሚና ግልፅ ባይሆንም በሩሲያና ዩክሬን መካከል እንደ አደራዳሪ ሆነው እያገለገሉ እንደሆነ ይሰማል።

የሳቸው ሚና "የተወሰነ" ነው ይላሉ የባለሃብቱ ቃል አቀባይ።

ባለፈው እሑድ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ሩሲያዊው ባለሃብት የሩሲያን ወረራ ለማርገብ እገዛ ማድረግ እሻለሁ እንዳሏቸው ተናግረው ነበር።

ሮማን፤ ከሞስኮው ኪዬቭ ብዙ ተመላልሰው የሰላም ድርድሩን ለማሳካት እንደጣሩም ተገልጧል።

ከእነዚህ ጉዞዎች በአንዱ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን አግንተዋቸው እንደነበር ነገር ግን ቃል አቀባያቸው ስለዚህ ግንኙነት የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተሰምቷል።

ቤሊንግካት የተሰኘው የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን እንደሚለው አብራሞቪችና ሌሎች አደራዳሪዎች ያጋጠማቸው መመረዝ "ከኬሚካል የጦር መሣሪያ" ጋር ግንኙነት ያለው ነው።

"የዓይን ሕመምና የቆዳ መሰነጣጠቅ" ከምልክቶቹ መካከል እንደሆነ ቤሊንግካት ዘግቧል።

አብራሞቪች ተመረዙ ከተባሉ ከ10 ቀናት በኋላ ባለፈው መጋቢት 14 እስራኤል ውስጥ ታይተዋል።

ሮማን አብራሞቪች ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት በአውሮፓ ሕብረትና በዩኬ መንግሥት ማዕቀብ እንደተጣለባቸው አይዘነጋም።

ነገር ግን አሜሪካ ሩሲያዊው ባለሃብት ለሰላም ድርድሩ ጠቃሚ ስለሆኑ እንዳትቀጣቸው ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ባይደንን መማፀናቸው ተገልጧል።

የሩሲያና ዩክሬን ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት ኢስታንቡል ውስጥ ተገናኝተው ድርድር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።