የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በአስቸኳይ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀረቡ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር ውጤት የሚያስገኝ የሰላም ንግግር በአስቸኳይ ማድረግ እንደሚፈልጉ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ለሕዝባቸው ባስተላለፉት በቪድዮ የተቀረጸ መልዕክት ላይ እንዳሉት በግዛታቸው ውስጥ ግዙፍ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች ካለችው ሩሲያ ጋር "ካለምንም መዘግየት ትርጉም ያለው" የሰላምና የደኅንት ንግግር እንዲጀመር ጠይቀዋል።

ይህም ሩሲያ በአገራቸው ላይ በከፈተችው ወረራ በፈጸመችው "ስህተት" የሚደርስባትን ጉዳት ለመቀነስ ያላት ብቸኛው እድል ነው ሲሉ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

"ለመገናኘት፣ ለመነጋገርና የዩክሬንን የግዛት አንድነት እንዲሁም ፍትህን ወደነበረበት ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንት ዜሌነስኪ ለሩሲያ ጥሪ አቅርበዋል።

"ይህ ካልሆነ ግን ሩሲያ ከሚገጥማት ውድቀት ለመውጣት በርካታ ትውልዶችን መጠበቅ ሊያስፈልጋት ይችላል" ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሐሙስ ዕለት ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት አገራቸው ጦርነቱን ለማቆም መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸው ተዘግቧል።

በዚህም ዩክሬን ማሟላት አለባት ከተባሉት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ዋናው የሩሲያ ፍላጎት ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን የሚጠይቅ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ዩክሬን ትጥቅ እንድትፈታ፣ በዩክሬን የሩሲያ ቋንቋ እንዲከበር እና የናዚ አመለካከት አራማጅ ናቸው የተባሉ ኃይሎችን ዩክሬን እንድትቆጣጠር፣ ክራይሚያ የሩሲያ ግዛት መሆኗን፣ በቅርቡ ነጻነታቸውን ላወጁት ምሥራቃዊ የዩክሬን ግዛቶች ደግሞ እውቅና እንድትሰጥ ዋነኞቹ የሩሲያ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።

ከሦስት ሳምንት በላይ የሆነው የሩሲያ ወረራ በዩክሬን ላይ ከተከፈተ በኋላ የሁለቱ አገራት መሪዎች ተገናኝተው በመወያየት ለጦርነቱ መፍትሔ እንዲገኝ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም አንዳች ነገር እስካሁን አልታየም።

ነገር ግን ባለፉት ሳምንታት የሩሲያና የዩክሬን ተጎራባች በሆነችው ቤላሩስ ውስጥ በሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ከሦስት ጊዜ በላይ ውይይት ቢደረግም ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችለ ውጤት ግን ሳያስገኝ ቀርቷል።

አስካሁን በበርካታ የዩክሬን ከተሞች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከባድ ውድመት የተከሰተ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን አገራቸውን ጥለው ወደ አውሮፓ አገራት ለመሰደድ ተገደዋል።