ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አራተኛው የሩሲያ ጀነራል ዩክሬን ውስጥ መገደልና የሩሲያ ጀነራሎች ኢላማ መሆን
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አራተኛ የሩስያ የጦር ጀነራል በዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን ተናገሩ።
ዜሌንስኪ ተገደሉ ያሏቸውን ጀነራል ስም ባይጠቅሱም የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ ግን የተገደሉት የጦር መሪ ሜጀር ጄኔራል ኦሌግ ሚትዬቭ ናቸው ብለዋል።
ጄኔራል ሚትዬቭ የተገደሉት በማሪዩፖል ከተማ አቅራቢያ መሆኑን የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የጀነራሉ መገደል አንዳንዶችን በዚህ ደረጃ ያሉ ከፍተኛ የጦር መሪ ለምን ለጦር ግንባር ቅርብ ሆኑ ብለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ወደ 20 የሚጠጉ ጀነራሎች በዩክሬን ያለውን የሩሲያ ጦር ዘመቻዎችን እየመሩ ይገኛሉ።
የአራተኛው ጀነራል ግድያ ከተረጋገጠ፤ ሩሲያ ለዚህ ጦርነት ካሰማራቻቸው ጀነራሎች አንድ አምስተኛው ተገድለዋል ማለት ነው።
አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚያምኑት ከሆነ እንዲህ ያለው ከፍተኛ ኪሳራ የሚፈጠረው ጀነራሎች በተሳሳተ ቦታ እና ጊዜ በመገኘታቸው ሳይሆን ዩክሬን በከፍተኛ የሩሲያ መኮንኖችን ላይ በማነጣጧሯ ነው።
የጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሪታ ኮናዬቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ይህ ድንገተኛ አጋጣሚ አይመስለኝም። አንድ አጋጣሚ ነው። ብዙ ሲሆን ግን ዒላማ ተደርገው ነው።"
አንድ የፕሬዝደንት ዜሌንስኪ የቅርብ ሰው ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩክሬን የሩስያ መኮንኖችን ለማጥቃት ብቻ የተቋቋመ ወታደራዊ የስለላ ቡድን እንዳላት ተናግረዋል።
"ከፍተኛ ጀነራሎች፣ አብራሪዎች እና የጦር አዛዦች ላይ ያተኩራሉ" ሲሉ ግለሰቡ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር በቁጥር ከመበለጡ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ማነጣጠሩ ለመረጃ ጦርነት አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ኮናዬቭ ተናግረዋል።
"ዒላማ የሚያደርግ አካል እንዳለ ማሰብ የዩክሬንን ሞራል ይመገባል። የድል አድራጊነት መንፈስ ነው። አበረታች ነው።"
የተወሰኑ የሩሲያ መኮንኖችን ዒላማ ለማድረግ ዩክሬን የት እንዳሉ ማወቅ አለባት። ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ አንዳንድ ዒላማዎች የት እንደሚገኙ ፍንጭ ሊሰጡ የሚችሉ የመገናኛ መንገዶችን ስትጠቀም ቆይታለች።
የሮቻን ኮንሰልቲንግ የመከላከያ ተንታኝ ኮንራድ ሙዚካ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ሩሲያውያን ከከፍተኛ መኮንኖቻቸው ጋር ለመገናኘት የሞባይል ስልኮችን ወይም የአናሎግ ሬዲዮዎችን እየተጠቀሙ ከሆነ ለዩክሬናውያን ሁሉም ነገር በእጃቸው ላይ ነው" ብለዋል።
ሜጄር ጄኔራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ የተባሉ ከፍተኛ መኮንን መገደላቸው ተክትሎ ሁለት የሩሲያ የደኅንነት መኮንኖች ስለ ጄኔራሉ ሞት ሲነጋገሩ እና ደኅንነቱ የተጠበቀው የግንኙነት አውታር አይሰሠራም ሲሉ የሚሰማበት ቀረጻ በዩክሬን በኩል ተለቋል።
በጦር ግንባር ላይ
እንዲህ ያሉ ከፍተኛ መኮንኖች ወደ ጦር ሜዳው በመቅረብ ራሳቸውን ለአደጋ ማጋለጣቸው ያልተለመደ ነገር ነው። የጦር መሪዎቹ ይህን እያደረጉ ያሉት ጦሩ ባቀደው መጠን ወደፊት መግፋት ሳይችል በመቅረቱ መሆኑን የምዕራባውያን ምንጮች ያምናሉ።
የጀነራሎቹ አሟሟት ግልፅ አይደለም። መረጃዎችን ከቦታው ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ሁሉም በግንባር ሲፋለሙ ተገኝተዋል የሚል ግምት ቢኖርም ይህ ግን የግድ አይደለም ይላሉ ኮናዬቭ።
"ይህ ማለት ጀነራሎቹ የግድ ግንባር ነበሩ ማለት አይደለም። ለምሳሌ ሲንቀሳቀሱ ወይም የአቅርቦት መስመሮችን ሲቃኙም ሊሆን ይችላል የተመቱት" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተገደሉ የሩሲያ ጄኔራሎች
ኦሌግ ሚትዬቭ። የ150ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩ።
ሜጀር ጀነራል ኦሌግ ሚትዬቭ እስካሁን ከፍተኛ ውጊያ በተደረገበት በደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘው ማሪዩፖል ከተማ አቅራቢያ መሞታቸው ተዘግቧል።
መቀመጫቸውም ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በሮስቶቭ ክልል ነበር።
አንድሬ ኮሌስኒኮቭ። የ29ኛው ጥምር ጦር አዛዥ የነበሩ።
እንደ ዩክሬን ባለሥልጣናት ከሆነ የ29ኛው ጥምር ጦር መሪ ሜጀር ጄኔራል አንድሬ ኮሌስኒኮቭ መጋቢት 11 በተካሄደ ጦርነት መገደላቸውን ገልጸዋል።
የግድያው ሁኔታ በዝርዝር አልተገለጸም።
ቪታሊ ጌራሲሞቭ። የ41ኛው ጥምር ጦር ዋና አዛዥ የነበሩ።
እንደ ዩክሬን መከላከያ ሚንስቴር ከሆነ የሩሲያ 41ኛው ጥምር ጦር ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ የካቲት 7 ከምሥራቃዊው ካርኪቭ ከተማ ውጭ ተገድለዋል።
ለሩሲያ ድንበር ቅርብ የሆነችው ካርኪቭ ከሩሲያ ጦር ያልተቋረጠ ጥቃት ደርሶበታል።
ጌራሲሞቭ በሁለተኛው የቼቺን ጦርነት፣ በሶሪያ የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ እና በ2014 ሩሲያ ክራይሚያን ወደ ግዛቷ ስታጠቃልል ተሳትፈዋል።
አንድሬ ሱክሆቬትስኪ። የ41ኛው ጥምር ጦር ምክትል አዛዥ የነበሩ።
ከጌራሲሞቭ ጋር በተመሳሳይ ክፍል ውስጥ ምክትል አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል አንድሬ ሱክሆቬትስኪ የካቲት 3 በአልሞ ተኳሽ መገደላቸው ተዘግቧል።
እንደ ጌራሲሞቭ ሁሉ ሱክሆቬትስኪ በክሬሚያ እና በሶሪያ ጦርነት የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ አካል ነበሩ።
ከሌሎቹ ጄኔራሎች በተለየ የሱክሆቬትስኪ ሞት በሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በንግግራቸው አንድ ጄኔራል በዩክሬን ስለመሞታቸውም አረጋግጠዋል።