ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካንዬ ዌስት ትሬቨር ኖዋን በመሳደቡ ከኢንስታግራም ታገደ
የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ካንዬ ዌስት በታዋቂው ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋ ላይ በሰነዘረው ዘር ተኮር ስድብ ምክንያት ከኢንሰታግራም ለ24 ሰዓታት ታገደ።
ሙዚቀኛው በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ላይ ተገቢ ያልሆ ነገር ያጋራው፣ የቀድሞ ሚስቱ በሆነችው ኪም ካርዳሺያን ላይ የፈጸመው ተግባር "አስፈሪ" ነው በማለት ኮሜዲያኑ ከተናገረ በኋላ ነው።
ካንዬ በተደጋጋሚ የቀድሞ ሚስቱን፣ ልጆቻቸውንና የአሁን አጋሯን ፒት ዳቪድሰንን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያሰፍር ቆይቷል።
የኢንስታግራም እና ሌሎች ግዙፍ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ባለቤት የሆነው ሜታ፣ ካንዬ ዌስት የጥላቻ ንግግርና ስድብን በሚመለከት የኢንስታግራም ደንቦችን ጥሷል ብሏል።
ኩባንያው ጨምሮም የበሰዎች ላይ ጉዳት የማድረስ ደንብንም ተላልፏል ሲል ነው ካንዬን ያገደው።
በዚህም ምክንያት ምንም እንኳን ሌሎች ሰዎች የካንዬን አካውንት ማየት ቢችሉም በገጹ ላይ የሚፈልገውን ነገር ማጋራት፣ አስተያየት መስጠት እና የቀጥታ መልዕክት መላክ አይችልም።
በቅርቡ ባሰፈው መልዕክቱ ላይ የቀድሞ ሚስቱ ኪም ልጆቹን እንዳያገኝ እንደከለከለችው የገለጸ ሲሆን፣ እሷ ግን ሐሰት ነው በማለት አስተባብላለች።
ሜታ ባወጣው መግለጫ ካኒዬ የማኅበራዊ መድረኩን ደንቦች መጣሱን የሚቀጥል ከሆነ "ተጨማሪ እርምጃ" እንደሚወስድ አመልክቷል።
"በተደጋጋሚ ደንቦቻችንን በሚጥሱ አካውንቶች ላይ እገዳዎችን በመጣል፣ ተጨማሪ እርምጃዎችን ሁልጊዜም እንወስዳለን" ብሏል ሜታ በመግለጫው ላይ።
እንዲሁም በካኒዬ ዌስት አካውንት ላይ ያሉ "ይዘቶች መሰረዛቸውን" ተገልጿል።
ትሬቨር ኖዋ፣ ለካኒዬ ዌስት ዘለፋ የዳረገውን አስተያየት የሰጠው "ዘ ዴይሊ ሾው" በተሰኘው ምፀታዊ የዜና ፕሮግራሙ ላይ ነበረ።
"ሀብታምና ታዋቂ ስለሆነች ለኪም ላታዝኑ ትችላላችሁ" ያለው ኖዋ "ነገር ግን እያለፈችበት ያለበትን ሁኔታ መመልከት አስፈሪ ነው" በማለት በርካታ ሴቶች ግንኙነታቸውን ሲያቋርጡ በሚገጥማቸው ፈተና ውስጥ በማለፍ ስኬታማ እንደሆነች ተናግሮ ነበር።
ስሙን በሕግ ወደ 'ዬ' የቀየረው ካንዬ ዌስት ከኪምና ከፒት ዳቪድሰን ጋር ያደረጋቸውን የጽሁፍ ምልልሶችን ፎቶዎች በማኅበራዊ መድረኮች ላይ በማጋራት ይፋ በወጣ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።
ትሬቨር ኖዋ ኪምን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት ላይ ካንዬ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ በሰጠው ምላሽ ዘርን የተመለከተ ስድብን አካቶ ነበር።
መልዕክቱም የኢንስታግራምን ደንብ የሚተላለፍ ነው ተብሎ እንዲነሳ ተደርጓል።