የብላክ ፓንተር ዳይሬክተር የባንክ ዘራፊ ተብሎ በስህተት ታሠረ

የብላክ ፓንተር ዳይሬክተር ራያን ኩግለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የብላክ ፓንተር ዳይሬክተር ራያን ኩግለር

ብላክ ፓንተር የተሰኘው ዝነኛ የልብ ወለድ ፊልም ዳይሬክተር የሆነው ግለሰብ ከባንክ ሒሳቡ ገንዘብ ሲያወጣ ተያዘ።

ራያን ኩግለር ከገዛ የባንክ ሒሳቡ 12 ሺህ ዶላር ሲያወጣ ተገኝቶ ነው በስህተት ዘራፊ ተብሎ በቁጥጥር ሥር የዋለው።

የባንክ ሠራተኛዋ ግለሰቡ ገንዘብ ሲያወጣ ስትመለከት ለአለቃዋ በመጠቆም ኩግለር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውል አስደርጋለች።

ኩግለር፤ ቲኤምዚ ለተሰኘው ጣቢያ "ይህ ፍፁም ሊሆን አይገባም ነበር" ሲል ተናግሯል።

ነገር ግን ብሏል የ35 ዓመቱ የፊልም ዳይሬክተር "ነገር ግን ባንክ ኦፍ አሜሪካ ሁኔታውን አስረድቶኝ ተግባብተን ተለያይተናል።"

ግለሰቡ ወደ ባንክ ሲገባ ለኮቪድ በሚል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም መነፅርና ኮፊያ አድርጎ ነበር።

ከዚያም ወደ ባንክ ሠራተኛዋ ተጠግቶ ከባንክ ሂሳቡ 12 ሺህ ዶላር አውጥታ እንድትሰጠው ጠየቃት።

ነገር ግን ለባንክ ሠራጠኛዋ በሰጣት ማስታወሻ ላይ ገንዘቡ ሰው ባልተሰበሰበበት ቦታ ላይ እንዲቆጠር እንደጠየቃት ተዘግቧል።

ኩግለር መታወቂያ ካርድ ሲጠየቅ ትክክለኛ መታወቂያ አቀብሏል።

ዳይሬክተሩ ገንዘቡን የፈለገው ለቤተሰብ ጤና ጉዳይ እንደሆነና መልኩ እንዳይታወቅ የፈለገው ደግሞ ከገንዘቡ ብዛት የተነሳ መሆኑን ለፖሊስ ተናግሯል ሲል ኒው ዮርክ ታይምስ ፅፏል።

ባንከኛዋ ልክ እንደ ኩግለር ጥቁር ስትሆን ነብሰ ጡር በመሆኗ በመስጋት ነው ሁኔታውን ለፖሊስ የጠቆመችው ሲሉ ጋዜጦች ዘግበዋል።

ከዚያ በኋላ ፖሊስ መጥቶ ዳይሬክተሩን በካቴና ጠፍሮት መታወቂያውን አይቶ ማንነቱን ካጣራ በኋላ ለቆታል።

ባንክ ኦፍ አሜሪካ ክስተቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ "ሁኔታው በመከተሰቱ ኩግለርን ይቅርታ እንጠይቃለን" ብሏል።

ብላክ ፓንተር የተሰኘው ፊልም በፈረንጆቹ 2018 ወጥቶ በርካታ ተመልካቾች አፍርቶ ነበር።