ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራዊያን ቢሊየነሩን ኢላን መስክ ኢንተርኔት እንዲያስገበላቸው እየተማጸኑ ነው
ትውልደ ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊዮነር ኢላን መስክ የኢንተርኔት አቅርቦት ለኤርትራ እንዲጀምር የኤርትራ ተወላጆች በስፋት እየጠየቁ ነው።
ቢሊየነሩ ኢላን መስክ በጦርነት ላለችው ዩክሬን ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠቱን ተከትሎ ነው ኤትርራዊያኑ በትዊተር እያደረጉት ባለው ማኅበራዊ ዘመቻ ለኤርትራም ተመሳሳዩን እንዲያደርግ እየጠየቁ ያሉት።
የስፔስኤክስ መሥራች ኢላን መስክ በቅርቡ ስታርሊንክ የተሰኘ የሳተላይት የኢንተርኔት ማቀባበያን ለዩክሬን አቅርቧል፡፡
የሩሲያን ወረራ ተከትሎ የኢንተርኔት መቋረጥ ቢኖርም ዩክሬናዊያን በስታርሊንክ አማካኝነት አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡
'ስታርሊንክ ለኤርትራ' (#Starlink4Eritrea) በሚል የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ቁልፍ ቃል በማስቀደም ጥያቄ እያቀረቡ ያሉት በብዛት በውጭ የሚኖሩ ኤርትራዊያን እና ትውልደ ኤርትራዊያን ናቸው፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር ኤርትራዊ ዳያስፖራ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይገኛል፡፡
ኤርትራ በኢንተርኔት አቅርቦት አለመኖር የተነሳ ዜጎች ከመረጃ ርቀዋል።
ኤርትራ በኢንተርኔት ሥርጭት በአፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ አቅርቦት ካለባቸው አገራት ቀዳሚዋ ናት፡፡ የኢንተርናሽናል ቴሌኮሚኒኬሽን ዩኒየን ባወጣው ሪፖርት የኤርትራ የኢንተርኔት ተደራሽነት በመቶኛ፣ ከ1 እጅ በታች ነው፡፡
ይህም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዝቅተኛ ከሚባሉት የሚመደብ ነው፡፡
በመንግሥት የተያዘው ኤሪቴል በአገሪቱ ብቸኛው የኢንተርኔት አቅራቢ ነው፡፡
በኤርትራ የሞባይል ዳታ (ኢንተርኔት) ስለሌለ ሕዝቦቿ ኢንተርኔት የሚያገኙት በዋይፋይ ብቻ ሲሆን ፍጥነቱም እጅግ ቀርፋፋ የሚባል ነው፡፡
እንደ ፌስቡክና ትዊተር የመሰሉ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ለመዝለቅም መንግሥትን ሊያስቆጣ ስለሚችል ዜጎች እንደ ቪፒኤን የመሰሉ መሽሎኪያዎችን ለመጠቀም ይገደዳሉ፡፡
ኤርትራ እንደ አውሮፓዊያኑ 1993 ወዲህ በአንድ ፓርቲና ግለሰብ የምትዘወር ምርጫ የማይካሄድባት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነጻ ሚዲያ የሌለባት አገር ናት፡፡
ባለፈው ሳምንት ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ የሩሲያን ወረራ ለማውገዝ ካልፈቀዱ አምስት አገራት አንዷ ነበረች፡፡
የቢሊየነሩ ኢላን መስክ ስታርሊንክ ዝቅ ባለ የህዋ ምህዋር የምትሾር ሳተላይት ስትሆን ያለ ምንም የፋይበር ዝርጋታ ሰዎች ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ ታስችላለች፡፡
ስታርሊንክ አገልግሎቱን ለማስጠት ምድር ላይ ካለ ጣቢያ ጋር ግንኙነት መፍጠር ይኖርባታል፡፡
ለዩክሬን እየቀረበ ባለው ኢንተርኔት ለምሳሌ ይህ ጣቢያ የተተከለው በጎረቤት ፖላንድ ውስጥ ነው፡፡