ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን ለሚሰማሩ ቅጠረኛ ወታደሮች በቀን እስከ 2ሺህ ዶላር ለመክፈል ማስታወቂያ ወጣ
የግል የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ቅጥረኛ ተዋጊ ወታደሮችን ለዩክሬን እየመለመሉ ነው።
አስቸኳይ ክፍት የሥራ ማስታወቂያ
የሥራ መደቡ መጠሪያ፡ ቅጥረኛ ተዋጊ
ተፈላጊ ችሎታ፡ ሁለትና ከዚያ በላይ ቋንቋ መናገር የምትችሉ፣ ቀደም ሲል በውትድርና አገልግሎት ውስጥ የነበራችሁ፣ ወደ ዩክሬን በሚሥጢር ዘልቃችሁ ለመግባት የፈቀዳችሁ፡፡
ደመወዝ ፡ በቀን 2ሺህ ዶላር (ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር)
የሥራ ሁኔታ፡- በጦርነት አደጋ ላይ የወደቁ ቤተሰቦችን ማውጣት
ከላይ ያነበባችሁት ከፊልም ቃለ ተውኔት የተወሰደ ይመስላል፡፡ አይደለም፡፡ የሥራ ቅጥር የሚፈጽም ድረ ገጽ ላይ የወጣ ትክክለኛ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ነው፡፡
ቅጥሩን ያወጡት ደግሞ የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ለደኅንነትና ጥበቃ ኩባንያዎች ይህ ጦርነት ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል፡፡ ተፈላጊነታቸውም በአያሌው ጨምሯል፡፡
ልዩ ኦፕሬሽን ከማካሄድ ጀምሮ የሎጂስቲክ አቅርቦት እስከ መስጠት ድረስ በውጊያው ይፈለጋሉ፡፡
በበጎ ፈቃድ ዩክሬን ሄደው ለመዋጋት ከአውሮጳ አገራት እየዘመቱ ያሉና ከዩክሬናዊያን ወታደሮች እኩል ይከፈለናል የሚሉት ሳይቀሩ በእነዚህ የግል ጥበቃ ኩባንያዎች ተፈልገው ጠቀም ያለ ገንዘብ እየተከፈላቸው ነው፡፡
ቀጣሪዎቹ ኩባንያዎች ዋና አገልግሎት የተሰጣቸው በኮንትራት ሲሆን እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር ኮንትራት የወሰዱ ኩባንያዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡
ዋናው ተልዕኮዋቸው በጦርነት ቅርቃር ውስጥ የገቡ ዜጎችን ደኅንነት ጠብቆ፣ ከጦርነቱ መንጋጋ በሰላም የማውጣት ሥራ ነው፡፡
ቶኒ፣ ሞዛይክ የሚባል መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ የደኅንነትና የጥበቃ ጉዳዮች አማካሪ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡
አሁን እሱ የሚመራው ኩባንያ በዩክሬን በሥራ ላይ ይገኛል፡፡
ክፍያን በተመለከተ እንደሚለው እያንዳንዱ ኦፕሬሽን እንደ ውስብስብነቱ እየታየ ዋጋውም በዚያው መጠን ይለያያል፡፡
‹‹ለምሳሌ በርካታ ሰዎችን ከጦርነቱ ቀጠና ማውጣት ከሆነ የመሞት ዕድሉም የዛኑ ያህል ነው፡፡ ሕጻናትና ሙሉ ቤተሰብ ማውጣትም ከባድ ሥራ ነው፡፡ ያሉበት ሁኔታ ዋጋውን ይወስነዋል›› ይላል፡፡
ሞዛይክ ኩባንያ ከጨበጣ ውጊያ ይልቅ የደኅንነት መረጃን ለቅሞ በማቅረብ ይበልጥ ይታወቃል፡፡
ሞዛይክን ጨምሮ ለብዙዎቹ የጥበቃ ኩባንያዎች ጦርነቱ ሰፊ የሥር ዕድል ይዞላቸው የመጣ ሲሆን በተለይ ዕውቅ ሰዎችን፣ ፖለቲከኞችን ከጦርነት ቀጠና ያለ ምንም እንቅፋት ይዞ በመውጣት ጥበብ ይታወቃሉ፡፡
የቅጥረኛ ተዋጋና አዋጊ ኩባንያዎች በዚህ ደረጃ ለሥራ ሲፈለጉ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡
ሆኖም ኅቡዕ ሆኖ የቆየ አገልግሎታቸው ይፋ የወጣው በኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነት ጊዜ ነው፡፡
በርካታ ምዕራብ አገራት እነዚህን ተዋጊና አዋጊ ቅጥረኛ የጥበቃ ኩባንያዎችን ቀጥረው ሲያሰሩ ተደርሶባቸዋል፡፡
በተለይ አሜሪካ ኢራቅን በወረራ በያዘችበት ወቅት እንደ ግዙፎቹ ብላክዎተር ያሉ የቅጥር ተዋጊ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡
መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እጅግ የከፋ የሰብአዊ ጥሰት ሲፈጽሙ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ሾልከው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ዊኪሊክስ የተወሰኑትን ለዓለም ካቀበለ ወዲህ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሰው ነበር፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች ቀጥታ የቅጥር ውጊያ ከማድረግ ባሻገር ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ወታደሮች ከሚገኙበት እጅግ አደገኛ የጦርነት አውድማ ድረስ ወስዶ ማቅረብ፣ የተጠኑ ውስብስብ ግድያዎችን መፈጸም ይጠቀሳል፡፡
የብላክዎተር ባልደረቦች በተለይ በ2007 በባግዳድ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተኩስ ልምምድ በማድረግ በተለይ 14 ንጹሐንን በመግደላቸው ስማቸው ሲብጠለጠል ኖሯል፡፡
በምሥራቅ አውሮጳ የቅጥር ተዋጊና ጥበቃ ኩባንያዎች ሥራቸው እጅግ የናጠጡ ሃብታሞችን መጠበቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የዩጎዝላቪያን መፈራረስ ተከትሎ በርካታ ተመሳሳይ ኩባንያዎች የቦስኒያና ክሮሺያን ታጣቂዎችን ማሰልጠን፣ ማስታጠቅና ተመሳሳይ አገልግሎተችን እንዲሰጡ ተቀጥረው ነበር፡፡
ይህም በአሜሪካ ፈቃድና እርዳታ የሆነ ነበር፡፡
የእነዚህ ኩባንያዎችን አገልግሎት በኅቡዕነታቸው የተነሳ እምብዛምም በዝርዝር ማወቅ ያስቸግራል፡፡
ይሁንና ይህ የቅጥር ተዋጊዎች ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እያደገ የመጣ የሥራ መደብ ሆኗል፡፡
የኤሮስፔስ እና ዴፌንስ ኒውስ ባወጣው አንድ መረጃ ይህ የሥራ መደብ እስከ 400 ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ሆኗል፡፡
ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ወይስ ኮንትራክተሮች
ብዙዎቹ ኩባንያዎች ራሳቸውን የሚጠሩት የጥበቃና ደኅንነት አገልግሎት ሰጪ ብለው ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ቅጥረኛ ተዋጊ ሆነን አንሠራም እያሉ አይናቸውን በጨው አጥበው ይክዳሉ፡፡
ይልቅ እኛ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በሰብአዊ ድርጅቶች ግብዣ አግልሎታችንን እንሰጣለን ሲሉ ያስተባብላሉ፡፡
ሆኖም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የእነዚህ ኩባንያዎች የሚወስዷቸው ኮንትራክተሮች ከቅጥር ግድያ እስከ መረጃ ለቀማ የሚዘረዘሩ ናቸው፡፡
በጦርነት ቀጠና ውስጥ ኮንትራት በመውሰድ የሚታወቀው ማይክ ሃውክ አሜሪካዊ ነው፡፡
እሱ ቅጥረኛ ገዳዮች ናችሁ ወይስ የጥበቃ ኮንትራክተሮች ለሚለው ጥያቄ ሲመልስ ‹እኔ የመለመልኳቸው ብዙዎች ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ የአስቸኳይ ሕክምና ባለሙያዎች ናቸው፤ ሆኖም መዋጋት የሚችሉ ናቸው፣ እኛ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች አይደለንም፡፡›› ይላል፡፡
በምዕራብ አገራት ያሉ እነዚህ ኩባንያዎች የአገሪቱን ሕግና ደንብ ተከትሎው የሚቋቋሙ ናቸው፡፡
ብዙዎቹ እውቅ ሰዎችን ጥበቃ ለመስጠት፣ የተወሰኑ ቁልፍ ቦታዎችን ለመጠበቅ ካልሆነ በቀጥታ ቅጥረኛ ሆነው ለውጊያ ኮንትራት አይወስዱም፡፡
ሆኖም ብዙዎች በዚህ ትንታኔ አይስማሙም፡፡
አልፎ አልፎ ከደኅንነት ጋር እንዲህ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ እና ተዋጊዎች ናቸው፡፡
ሚስተር ማየር በዘርፉ አዋቂ የሚባሉ ናቸው፡፡ እሳቸው ግን ይህን ይላሉ፡፡
‹‹ብዙ ሰዎች ስለሕጋዊነትና ሞራል ያወራሉ፤ ኩባንያዎቹ ጦር አውድማ ነው የሚገቡት፤ ሁሉንም ነው የሚሠሩት፤ በአፍሪካ ውስጥ ኮንትራት ወስደው ይዋጋሉ፡፡ አስፈላጊ ሲሆንም ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ይሆናሉ፡፡ በሕጋዊነትና በሕገ ወጥነት መሀል ያለው መስመር ደብዛዛ ነው፡፡››
ከነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ስም ያላቸው ደቡብ አፍሪካ መቀመጫውን ደረገው ኢክስኩይቲቭ አውትካም ይጠቀሳል፡፡
በ90ዎቹ በአንጎላና ሴራሊዮን መንግሥት ኮንትራት ተሰጥቶት የተዋጋ ኩባንያ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት አቀነባብሮ እስከመምራት ይደርሳሉ፡፡
የሩሲያ ገዳይ ቡድንም ስመ ገናና ነው፡፡
በርካታ ኮንትራቶችን በሶሪያ የፈጸመ ሲሆን አሁን ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ እንደሆነ ይነገራል፡፡