አውስትራሊያዊው ታዳኝ ወንጀለኛ ከ12 ዓመታት ፍለጋ በኋላ ተያዘ

አውስትራሊያ በአገሪቱ ውስጥ ቀንደኛ ወንጀለኛ የሆነውንና ለአስራ ሁለት ዓመታትም ስታድነው የነበረችውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታውቃለች።

የ64 ዓመቱ ግርሃም ፖተር በቀረበበት የግድያ ማቀነባበር ሴራ ወንጀል ክስ በቪክቶሪያ ግዛት በሚገኘው ፍርድ ቤት አለመቅረቡን ተከትሎም ነበር ፖሊስ ሲያድነው የነበረው።

ግለሰቡ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በሽሽት ላይ ነበር።

የቀረበበት ክስም ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ንግድ አለመግባባት ጋር በተገናኘ የአንድ ወሮበላ ቡድን አባላት ግድያዎችን ለመፈጸም ከተመለመሉት መካከል አንዱ እንደነበር አትቷል።

ፖሊስ ግለሰቡ ኪውንስላንድ በሚባል ስፍራ እንደሚገኝ ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ባደረገው ክትትል በያዝነው ሳምንት ሰኞ ሊይዘው ችሏል። በማኅበራዊ ትስስር የወጣ ቪዲዮ ግለሰቡ በካቴና ታስሮ ሲወሰድ ያሳያል።

ፖተር ከዚህ ቀደምም በአስራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ታዳጊን ጭንቅላት ቆርጦ በመግደል በአውሮፓውያኑ 1981 የዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶበት ነበር። የእስር ጊዜውን፣ 15 ዓመታት ጨርሶ ከእስር ተፈትቷል።

ግለሰቡ በተደበቀበት ወቅትም ከግድያ ማቀነባበር ሴራ ወንጀል ክስ በተጨማሪ ግምታቸው 317 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ኮኬይንና ኤክስታሲ የተሰኙ አደንዛዥ ዕፆችን በማዘዋወር የፌደራል ክስ ቀርቦበት ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመላ አገሪቱ በርካታ ያልተሳኩ ጥቆማዎች የነበሩ ሲሆን ነገር ግን ፖሊስ በአውሮፓውያኑ 2017 ፖተርን ለመያዝ እያደረገው ባለው ፍለጋ "ተስፋ ቆርጧል" ሲል ዘ ኤጅ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅትም ግለሰቡን በማስያዝ አስተዋፅኦ ላደረጉና ለፖሊስ ጥቆማ ለሰጡ ግለሰቦች የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ፖተር ማንነቱ እንዳይታወቅ በሚል መልኩን እና ባህሪውን ለመቀየር ሞክሮ እንደነበር ያስታወቀው ፖሊስ በተያዘበት ወቅትም በአካባቢው የፀጉር ማቅለሚያም መገኘቱም ተገልጿል።

"ለረዥም ዓመታት በከባድ ወንጀል ስንፈልገው የነበረውን ግለሰብ በመያዝ ጉዳዩ መቋጫ አግኝቷል" በማለት በቪክቶሪያ የወንጀል ትዕዛዝ ተጠባባቂ ረዳት ኮሚሽነር ሚክ ፍሬወን ተናግረዋል።

ፖተር ወደ ቪክቶሪያ ተላልፎ የሚሰጥ ሲሆን በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባል።