ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለአስርተ ዓመታት 'በሺህ የሚቆጠሩ' ሰዎችን አፈር ያቀመሱት የደሴ ከተማ ነዋሪ
እዚህ ምድር ላይ ከሚያስደነግጡም ከሚያስፈሩም ነገሮች አንዱ ሞት ነው። ሞት አይደለም ግብሩ፤ ስሙ ሲጠራ ከመፍራታቸው የተነሳ ብርክ የሚይዛቸው፣ ዓይናቸው እንባ የሚያቀር ጥቂት አይደሉም።
ከራሳቸው ሞት ይልቅ የሚወዱትን ሰው ማጣት የሚያሸብራቸውም ብዙዎች ናቸው።
አሁን አሁን እዚህም እዚያም በአሟሟትም ሆነ በሟች ብዛት ስሙ ተበራክቶ ለጆሮ ቢለመድም፤ ሞት ሁልጊዜ አስደንጋጭ፤ ሁልጊዜ አዲስ ነው። ይህ ሞትን አብዝተው የሚፈሩትን የአጋፋሪ እንደሻውን ታሪክ ያስታውሰናል።
እዚህ ላይ "አጋፋሪ እንደሻው ደግሞ ማን ናቸው?" ማለታችሁ አይቀርም።
አጋፋሪ እንደሻው ብዙዎቻችን ለሞት ያለንን ስሜት ተላብሰው የተደረሱ የደራሲ ስብሃት ገ/ እግዚአብሔር ገጸ ባህርይ ናቸው። ልቦለዳዊ ታሪካቸው 'በአምስት ስድስት ሰባት' መጽሐፍ ውስጥ ተከትቧል።
በድርሰቱ ውስጥ አጋፋሪ እንደሻው ሞትን በመሸሽ ሞትን ለማምለጥ የሞት ሽረት ትግል የሚያደርጉ ገጸ ባህርይ ናቸው። ሞትን ማምለጥ ግን እንደምን ይቻላል?
ደራሲ አዳም ረታ በ'እቴሜቴ ሎሚ ሽታ' መጽሐፉ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔርን ስለእኚህ ገጸ ባህርይ [አጋፋሪ እንደሻው] በምናብ አናግሮት ነበር።
ስብሃትም በምናብ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጥቶታል።
"የሰው ልጅ ሥራው ከሞት ማምለጥ ነው እናም ከሞት የሚሸሹ ሰውዬ ታሪክ እየጻፍኩ ነው። ሰው የተሰራው ለሞት ነው። አጨራረሱ ሁልጊዜ ሞት ነው። ከሞት የማምለጥ ጥረቱ ይጻፋል። ሁሉም ነገር ጥረት ነው። ሰው ሞትን በተለያየ ጊዜ በተለያየ ስልት በዓመታት፣ በሰዓታትና በደቂቃ ይሸውዳል።
"የተለያየ ዓይነት የመኖር ጥረት አለ። አንዳንዱ ያለፍቅር ይኖራል። አንዳንዱ ሌላውን በመግደል ወይም ሌላውን በማጥፋት ለብዙ ዘመን መኖር ይፈልጋል። አንዳንዱ ዝም ብሎ ለዘላለም ልኑር ይላል። አንዳንዱ ብዙ ለመኖር ፈጣሪን ይለምናል። አንዳንዱ ሞትን ሊያሸንፍ ጥሩ ይበላል፤ ጥሩ ይጠጣል። እና አጋፋሪ እንደሻው ነገረ ሥራቸው ማንንም ይመስላል። ብዙ ሰዎችን ይመስላል። . . . "
የደሴ ከተማ ነዋሪው አብዱ ፋጤም በጎ ሥራቸውን ሲከውኑ ለሞት የሚደረግ ትግልንና ሞት እምቢነትን ተመልክተዋል።
አብረዋቸው ሲጫወቱ የነበሩ ሰዎች ጨዋታቸውን እንኳን ሳይቋጩ ድንገት ሲያልፉ አይተዋል። ለሞት ቀጠሮ ይዘው፣ "ዛሬን እንኳን አላልፍም" ብለው የተሰናበቱም ገጥመዋቸዋል። እንደ ድንገት በወጡበት የቀሩም እንዲሁ።
"በአማን ያሳድረን" ብለው በተኙበት ሞት የወሰዳቸው እንዳሉ ሁሉ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡም አሉ።
አብዱ በሞት ግብ ግብ ውስጥ ለመኖር የሚደረግ መንፈራገጥንም ታዝበዋል።
አብዱ ሞትን እንደመወለድ ነው የሚያዩት። ልክ ስንወለድ አብሮ እንደተፈጠረ የሕይወት ሌላ ክስተት። የሞትና የሕይወትን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታነትም በዓይነት በዓይነቱ አይተውታል።
"ሞት አብሮን ነው ያለው፤ በእኛ ላይ መቼ የበላይነት እንደሚቆናጠጥ ነው የማናውቀው" ይላሉ አብዱ።
ስለሆነም እንደ አጋፋሪ እንደሻው ሞት አያስበረግጋቸውም።
በእርግጥ አብዱ እናታቸውን በሞት ሲያጡ እጅጉን ደንግጠው፤ በጣሙንም አዝነው ነበር። ከእናታቸው ጋር የጓደኛ ያህል ቅርብ ነበሩ።
ለዚያም ነው ፋጤ የሚለው የእናታቸው መጠሪያ የስማቸው ተከታይ የሆነው። እናታቸውን አብዝተው ስለሚወዱ ነው የአካባቢው ሰው አብዱ ፋጤ እያሉ የሚጠሯቸው። በትክክለኛ የመዝገብ ስማቸው ግን አብዱ ከማል ነው የሚባሉት።
"ሞትን አስደንጋጭ የሚያደርገው ከሟች ጋር ያለን ግንኙነት ነው" ይላሉ አብዱ። ለእርሳቸው ደግሞ ከእናታቸው አብልጠው የሚቀርቡትም ሆነ የሚወዱት ሰው አልነበረም።
አብዱ እናታቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ ግን ሞት እንደ ከዚህ ቀደሙ አስደንግጧቸው አያውቅም።
ሞት መቼ እንደሚጎበኛቸው ባያውቁም "ሁሌም ተዘጋጅቼ ነው የምጠብቀው" ይላሉ።
አብዱ በአንዲት አነስተኛ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት። በከተማው የሚታወቁት ቀባሪ የሌላቸውንና በአደጋም ሆነ በሌላ አጋጣሚ እንደዘበት ወጥተው የቀሩ ሰዎችን አፈር በማቅመስ ነው።
በአነስተኛ ጎጇቸው ሃብት ንብረት የላቸውም። ቃሬዛ፣ መቆፈሪያ እና ሰው ለመቅበር የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ግን ሁሌም በቤታቸው ዝግጁ ናቸው።
የአስክሬን ከፈኖችንም የሴት፣ የወንድ፣ የሙስሊም፣ የክርስቲያን ብለው አሰናድተው ነው የሚያስቀምጡት።
እነዚህን ቁሳቁሶች የሚያገኙት በበጎ ፈቃድ ልገሳ ነው።
አብዱ በእምነታቸው ሙስሊም ቢሆኑም የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚፈፅሙት ግን የሌላ እምነት ተከታይ ለሆኑትም ጭምር ነው።
በቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት የሚደረጉ ሥርዓቶችን በእምነታቸው ተምረዋል። የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ሟቾችንም ከእምነቱ ተከታዮች ጋር ሆነው ይቀብራሉ።
በከተማው በዚህ በጎ ሥራቸው ነው የሚታወቁት።
በሆነ አጋጣሚ ሕይወታቸው ያለፉና ቀባሪ ያጡ ሰዎች ካሉ ስልክ የሚመታው ወደ ማዘጋጃ ቤት ሳይሆን ወደ እርሳቸው ነው። ከዚያም አንስተው ሙስሊሙንም ክርስቲያኑንም በወግ ይቀብራሉ።
ወደዚህ በጎ ሥራ እንዴት ገቡ?
አብዱ አሁን 50 ዓመታቸው ነው። ወደዚህ በጎ ሥራ የገቡበት ጊዜ አስርት ዓመታትን ወደ ኋላ ይወስደናል። ጊዜው 1988 ዓ.ም ነው። አጋጣሚው ደግሞ የአንድ ጓደኛቸው ቀባሪ ማጣት።
"ከብሔራዊ ውትድርና እንደተመለስን አንድ ጓደኛችን በመኪና አደጋ ሞተ። የሚቀብረው አጣ። እኔም 'አፈር ነኝ' እንዴት ይህ ሰው ቀባሪ ያጣል ብዬ ሃዘን ገባኝ" ይላሉ በወቅቱ የተፈጠረውን ሲያስታውሱ።
ከሞቱ ይልቅ ቀባሪ ማጣቱ አሳዘናቸው። በወቅቱ የቀብር አፈጻጸም እውቀቱም ሆነ የሚያስፈልጉት ቁሳቁሶች አልነበራቸውም።
በዚህ ምክንያት የጓደኛቸው አስክሬን ሳይቀበር አደረ። በማግስቱ የሚያስፈልገውን አድርገው የቀብር ሥነ ሥርዓቱን እንደነገሩ ፈፀሙ።
በዚህ አጋጣሚ ነው ይህን በጎ ሥራ ለመስራት ለራሳቸው ቃል የገቡት።
ከዚያን ጊዜ በኋላ ሥራዬ ብለው ቀባሪ ያጡትን በፈቃደኝነት አንስተው ይቀብራሉ።
"እስካሁን ከ4000 በላይ ሰዎችን የቀብር ሥነ ሥርዓት ፈጽሜያለሁ" ይላሉ። ታዲያ ብቻቸውን አይደለም። በበጎ ሥራ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እገዛ ተጨምሮበት ነው።
"ሞት አሳዛኝ ነው፤ በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ሰውን ያህል ነገር ጣል አድርገሽ ስትመለሽ ያሳዝናል፤ ግን በሥራዬ እርካታ አገኛለሁ፤ ከዚህ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም" ይላሉ አብዱ።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን የሚፈፅሙላቸውን ግለሰቦች ስም ዝርዝርም መዝግበው ይይዛሉ። ይህን የሚያደርጉት ዘግይተው የሰሙ የሟች ቤተሰቦች አስክሬናቸውን አውጥተው በፈለጉበት ቦታ ማሳረፍ ከፈለጉ በሚል እሳቤ ነው።
ለአብዱ 'ሞት' ምንድን ነው?
ሰው አኗኗሩ ብቻ አይደለም የሚያስጨንቀው። አሟሟትና አቀባበሩም ያሳስበዋል። ለዚያም ነው ከጸሎታችን 'አሟሟቴን አሳምርልኝ፤ ቀባሪ አታሳጣኝ' የሚል ቃል የማይታጣው። በባህልና በእምነት መሠረት በወግ መሸኘትም ክብር ነው።
አብዱም ከሞት ይልቅ የሚያሳስባቸው ይህ ነው።
"ሞት ሁልጊዜ እንዳለ አውቃለሁ። ስቀመጥም፣ ስነሳም፣ ስሄድም ሞት እንዳለ አውቃለሁ። ከፈን አጠገቤ አድርጌ ነው የምተኛው። ሁሉም ሂያጅ ነው። ምንም አልፈራም። ተረኛ ነኝ በተራዬ እንደምሄድ አውቃለሁ" ይላሉ።
ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጥረት ግን ከሞተ በኋላ በወግ አፈር መልበስ አለበት የሚል አቋም አላቸው።
በመሆኑም አብዱ አንድ ሰው እንዴትም ሆኖ፣በምንም ዓይነት አጋጣሚ ሕይወቱ ቢያልፍ አስተካክለው ከመቅበር ወደ ኋላ አይሉም። ሰቅጣጭ እና ዘግናኝ አሟሟትንም አይጠየፉም።
"የእኔንስ መጨረሻ ማን አወቀው ?" ይላሉ።
"በቀን ሦስትና አራት ሰው እቀብራለሁ" የሚሉት አብዱ አደጋ ሲያጋጥም ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ተናግረዋል።
ለዚህ በጎ ሥራቸው ግን የሚከፈላቸው ቤሳቤስቲን የለም።
የህወሓት አማጺያን ደሴ ከተማን ተቆጣጥረው በነበረ ሰዓት
አብዱ የህወሓት አማጺያን ደሴ ከተማን ተቆጣጥረው የነበረበት ወቅት ለእርሳቸውና ለሌሎች በጎ ፈቃደኞች ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ጦርነቱን ሽሽት በርካታ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል። ማዘጋጃ ቤትን ጨምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል።
እድርና ቅሬም ቢሆን እንደቀድሞው ማኅበራዊ ፋይዳቸው ጠንካራ አልነበረም።
የህክምና ተቋማትም አገልግሎታቸውን አቋርጠው ስለነበር "ቤታቸው ውስጥ በመድሃኒትና በህክምና እጦት ሕይወታቸው ያለፈና ቀባሪ ያጡ ሰዎች ነበሩ" ይላሉ።
ታዲያ በዚህ ጊዜ የሚነገራቸው ለእርሳቸው ነበር።
የስልክ አገልግሎትም ስላልነበር የአካባቢው ልጆች ቤታቸው ድረስ በመሄድ ነበር የሚነግሯቸው።
"በህመም ብቻ ሳይሆን በጥይት የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎችም [ የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር] ነበሩ" የሚሉት አብዱ በቀን እስከ አምስት የሚደርሱ ሟቾችን የቀብር ሥነ ሥርዓት ይፈፅሙ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን መፈፀምም ቀላል አልነበረም።
"ለአንድ ሰው ቀብር እንዴት 20 ሰው ይገኛል" በሚል ከአማጺያኑ ጋር ግብግብ የገጠሙበትን አጋጣሚ አንስተዋል።
አብዱ እንደሚሉት ደሴ ከተማ በአማጺያኑ ሥር በቆየችበት ከአንድ ወር በላይ በሆነ ጊዜ 200 ገደማ ሰዎችን የቀብር ሥነ ሥርዓት ፈፅመዋል።
"ብሞት የሚቀብረኝ ዘመድ የለኝም። እርሱ ይቀብረኛል ብዬ ነው ተስፋ ያደረኩት"
እቴነሽ ብርሃኑ የአብዱ ጎረቤት ናቸው። ባለቤታቸው በሕይወት ሲያልፉ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን በክብር የፈፀሙላቸው አብዱ ናቸው። " አብዱ ሩህሩህ ነው። አዛኝ ነው" ይላሉ።
"አብዱ ያገኘውን አካፍሎ የሚኖር ሰው ነው። የቸገረው፣ የራበው አይወድም። ለራሴ ልብላ አይልም። ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም አዛኝ ነው" ያሉት ደግሞ የ80 ዓመት አዛውንት ጎረቤታቸው አበበች ሙሳ ናቸው።
እኝህ እናት " እኔ ሞት የምጠብቅ ሰው ነኝ ፤ ብሞት የሚቀብረኝ ዘመድ የለኝም። እርሱ ይቀብረኛል ብዬ ነው ተስፋ ያደረኩት" ብለዋል።
አብዱ በዚህ በጎ ሥራቸው በክልሉ መንግሥት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ከተለያዩ ማኅበራትና ድርጅቶችም የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን፤ የ2013 ዓ.ም የደሴ ከተማ አስተዳዳር የበጎ ሰው ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል።