ኤርትራዊት-ጣሊያናዊቷ ማሪያ ለፍቅር የከፈለችው መስዋዕትነት

ወቅቱ እንደ አውሮፓውያኑ 1941 ነበር። የ18 አመቷ ማሪያ ማኔቲ የብሪታንያ መኮንን ከሆነው ፍቅረኛዋ ጋር ለመሆን ህይወቷን ሊያሳጣት የሚችል መስዋዕትነትን ለመክፈል ውሳኔ ላይ ደረሰች።

እንዴት? መጀመርያ ትንሽ ስለማሪያ እንንገራችሁ።

ማሪያ ማኔቲ የሁለት ሃገሮች፣ ባህሎችና ማንነቶች ባለቤት ናት፣ ኤርትራዊት እና ጣሊያናዊት። ከጣሊያናዊ አባት እና ወይዘሮ ስላስ ገብረፅዮን ከተባለችው ኤርትራዊት እናት በአውሮፓውያኑ 1923 ኤርትራ ውስጥ ተወለደች።

እናቷ እምኒ ፀሊም የምትባል መንደር ነው ትውልዳቸው የሚመዘዘው።

የማሪያ ከጣልያን አባት መወለድ ከኤርትራ ታሪክ አንፃር አዲስ ነገር አይደለም። ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ግዛት የተገዛችው በአውሮፓውያኑ 1890 ነው።

በሚቀጥሉት ስድስት አስርት አመታትም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት በኤርትራ ተቀማጭነታቸውን ካደረጉ የጣሊያን ወንዶች ተወልደዋል። እነዚህ ጣሊያናዊ ወንዶች ለልጆቻቸው እውቅና አልሰጧቸውም፤ እንደነፈጓቸው ነው የቀሩት።

የማሪያ ውልደትና ማንነትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።

ስለማሪያ ትንሽ ካልናችሁ ህይወቷን ሊነጥቃት ወደነበረው የፍቅር ታሪክ እንመለስ።

ይህ ታሪክ 'ዌስተርን ሞርኒንግ ኒውስ' በተሰኘው ጋዜጣ 'ሰቨን ሃንድረድ ማይል ኢን ኤ ቦክስ' በሚል ለንባብ በቅቷል።

በጋዜጣው ላይ ለንባብ የበቃው ታሪክ ማሪያ ከኤርትራ መዲና አስመራ እንዴት እንደወጣችና ከፍቅረኛዋ እንግሊዛዊው መኮንን ጋር አብራ ለመሆን የከፈለችውን ከፍተኛ ዋጋ ይዘረዝራል።

የሁለቱ ፍቅረኞች ታሪክ የሚጀምረው በአውሮፓውያኑ 1941 ነው። ወቅቱ የእንግሊዝ ጦር አዲስ አበባ ከገባ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መሆኑ ነው። ማሪያ ከፍቅረኛዋ ጋር የተዋወቁት በእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ነው። ያኔ እድሜዋ ገና አስራ ስምንት ነበር።

የጋዜጣው ዘጋቢ ማሪያና በወቅቱ አግብታው የነበረውን ባለቤቷን ያገኛቸው ግን ከአምስት አመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1946 ነበር።

ዘጋቢው በታሪኩ ላይ ስሙ ያልተጠቀሰው ባለቤቷና ማሪያን ያገኛቸው በዩናይትድ ኪንግደም ኮርንዌል ውስጥ በምትገኝ የባህር ዳርቻ መንደር ፖርትስካቶ ውስጥ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ነው።

ማሪያ የ24 አመት ወጣት ነበረች። አንድ አመት ከስምንት ወር የሆነውን ዴቪድ የተባለውን ልጇን ይዛ ነበር።

ትውስታው ስምንት አስርት አመታትን ወደኋላ ይወስደናል፤ ወደ በአውሮፓውያኑ 1941። ያኔ ኤርትራ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነበረች።

ሌተናል ጄኔራል ዊልያም ፕላት በሱዳን ቅጥረኛ ተዋጊዎች በመታገዝ ወደ ኤርትራ ምዕራባዊ ክፍል ወደሆነችው ከረን እየገፉ ነበር። ከረን በእንግሊዝ ጦር ቁጥጥር ከገባች ከሶስት ወራት በኋላም አስመራንም የእንግሊዝ ጦር ተቆጣጠራት።

በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ የታሪክ ድርሳናት ሲቃኙት ጣሊያኖች 'ላ ፒኮላ ሮማ' (ትንሿ ሮም) ብለው በሚጠሯት አስመራ ከትመው፣ ኑሯቸውን አደላድለው ነበር። ምናልባት ይህ ሁኔታ ለብሪታንያ አስደናቂ ሊሆን ይችላል።

የማሪያ ታሪክ ከነበረው ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተወሳሳበ፣ ፍፁም የተዘበራረቀ ነበር። የጣሊያን ወታደሮች እየሸሹ ነበር። በጣሊያን የተመለመሉት የአገሬው ነዋሪ ወታደሮች ወይም አስካሪስ ተበታተኑ። የአገሪቷም ምጣኔ ኃብትም በፍጥነት ማሽቆልቆል ጀመረ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የሚገርመው ጉዳይ ኤርትራ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ብትሆንም በወቅቱ አገሪቱ እየተመራች የነበረው በጣሊያን ቢሮክራቶች መሆኑ ነበር።

ለዚህም ምክንያቱ እንግሊዞች ሀገሪቱን ለማስተዳደር የሚያስችል በቂ የሰው ሃይል አልነበራቸውም።

ሚሼላ ዎንግ 'አይ ዲድንት ዱ ኢት ፎር ዩ ሃው ዘ ወርልድ ቢትሬይድ ኤ ስሞል አፍሪካን ኔሽን ' (I Didn't Do It for You: How the World Betrayed a Small African Nation) በሚል መፅሃፋቸው በኤርትራ ውስጥ የነበረውን የምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች እሽቅድድም እንግሊዞች የጣሊያንን ጦር ለመምታት እንጂ የኤርትራን ህዝብ ነፃ ለማውጣት እንዳልነበረ ያስረዳሉ።

የማሪያ አስደናቂ የፍቅር ታሪክ

የጣሊያን ወታደሮች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ከአገሬው ሴቶች የወለዷቸውን ልጆችም ጥለው ነው የወጡት። ለፍቅር ስትል ህይወቷን አደጋ ላይ የጣለችው ማሪያ ህይወትም በዚያን ጊዜ ከነበረው ክስተት ጋር ተገጣጠመ።

በስለላ ስራ ላይ የተሰማራው የማሪያ ፍቅረኛ በአስመራ የነበረው ቆይታ አጭር ነው። በአውሮፓውያኑ 1942 መጋቢት ወር ላይም ወደ ግብፅ ተዛወረ።

ነገር ግን ማሪያን ትቶ መሄድ አልፈለገም። ግራ ያጋባው ነገር እንዴት አድርጎ እንደሚወስዳት አለማወቁ ነበር።

ጣሊያናዊ በመሆኗ ህጋዊ በሆነ መንገድ ሊወስዳት አልቻለም። ጣሊያኖች በሙሉ በስለላ ይጠረጠሩ ስለነበር ሌላ መንገድ መቀየስ ነበረበት።

ከጥቂት አመታት በኋላ በታተመው ታሪክ መሰረት መኮንኑ ማሪያን ከአገር ለማስወጣት በእጁ ላይ ያሉትን ሁለት አማራጮች ማመዛዘን ጀመረ። የመጀመሪያው አማራጭ ማሪያ ፊቷን ሸፍና የአካባቢውን ሴት መስላ የሱዳንን ድንበር ማቋረጥ ነው።

ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ማሪያ ከእሱ ጋር በድብቅ እንድትጓዝ ማድረግ ነበር።

በመጨረሻም ሁለተኛው አማራጭ ቀለል ሆኖ አገኘው። ማሪያን ካማከረ በኋላ እቅዱ የነበረው ከአስመራ ወደ ሱዳን ከዚያም ወደ ግብፅ በባቡር እና በጭነት መኪና በድብቅ እንድትጓዝ ነበር።

ለዚህም የተመረጠው ትልቅ ሳጥን ነበር። ከአገር ከመውጣታቸው በፊት፣ ሁለት ተኩል በሁለት ተኩል ጫማ ስፋትና ሶስት ተኩል ጫማ ርዝመት ያለው ሳጥን ገዝቶ መኝታ ክፍሉ ውስጥ አስገባው።

አብሮት የሚኖር አንድ ግለሰብ ስለነበረም የጉዟቸው ዋዜማ ላይ በነበረው ምሽት ማሪያን ወደ ክፍሉ በድብቅ ማስገባት ነበረበት። ማሪያ የመጀመሪያውን ምሽት በሳጥኑ ውስጥ ማሳለፍ ነበረባት።

ጉዞ በሳጥን ውስጥ

በማግስቱ ሳጥኑ በባቡር ተጭኖ 80 ማይል (129 ኪሎሜትር) ተጉዞ ወደ ኤርትራ ምዕራባዊ ክፍል አጎርዳት ደረሰ። ጉዞውም 24 ሰአት የፈጀ ነበር።

ማሪያ ቃለ መጠይቅ ላደረገላት ጋዜጠኛ ታሪኳን በነገረችው ወቅት በሳጥን ውስጥ የተጓዘችበትን ያንን ትውስታ ሙሉ በሙሉ ከጭንቅላቷ ማጥፋት እንደምትፈልግ ነግራዋለች። በጉዞው ላይ በከፍተኛ የሆድ ቁርጠት እየተሰቃየች ነበር።

እንደ እድል ሆኖ ልቧን ለማነቃቃት ሁለት መርፌዎችን ጭኗ ላይ መወጋት ነበረባት።

ከአጎርዳት በመቀጠል በሱዳን ድንበር ላይ ወደምትገኘው ከሰላ 90 ማይል (145 ኪሎሜትር) በሳጥን ውስጥ ሆና ተጓዘች።

በዚህ ወቅት ጉዞው በኮረኮንች መንገድ ላይ ሲሆን የቀኑ ሙቀት ደግሞ ሌላ መከራ ነበር የሆነባት ። በዚያ ፈታኝ መንገድ ላይ 130 ዲግሪ የሚጠብስ የፀሃይ ሙቀት ተጨምሮበት መቋቋም ተስኗት እንደነበር ማሪያ ታስታውሳለች።

በካርቱም የተደቀነው ችግር

ሳጥኑ ካርቱም ከደረሰ በኋላ መኮንኑ ፍቅረኛዋ በሳጥን ታፍና እየተጓዘች ያለችው የማሪያ ሁኔታ በጣም አስጨነቀው።

ህይወቷም አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል በማሰብ በጣም ፈራ። ይህንንም አስቦ ሳጥኑ እንዲወርድና እንዲራገፍ ጠየቀ። ነገር ግን ሳጥኑን አውርዶ ለማራገፍ ፈቃድ አልነበረም።

እናም መኮንኑ ይህንን ሲረዳ በባቡር ጣቢያው ላይ ችግር በመፍጠሩ በቦታው የነበሩት ወታደራዊ ፖሊሶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት።

ፖሊስ ጣቢያ ከደረሰ በኋላም በጭንቀት የተወጠረው መኮንን እውነቱን ለመናገር ወሰነ። ፍቅረኛው ማሪያ ሳጥን ውስጥ እንዳለችና ታፍና ልትሞት እንደምትችል ነገራቸው። ፖሊሱ ማሪያን ለማዳን በፍጥነት ወደ ጣቢያው ተመለሰ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መኮንኑ ፖሊስ ጣቢያ በነበረበት ወቅት የባቡር ጣቢያው ሰራተኞች ሳጥኑን መሬት ላይ ሲያወርዱ ጭንቅላቷ ወደታች ተዘቀዘቀ።

እንደ ማሪያ ገለጻ ለ20 ደቂቃ ያህል በዚህ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ውስጥ ቆየች። ደርሰውም ሳጥኑን በከፈቱበት ወቅት ራሷን ስታ ነው የተገኘችው። በጣም ተጎድታም ነበር።

"ስነቃ ራሴን ያገኘሁት በሆስፒታል ውስጥ በዶክተሮች ተከብቤ ነው።" ብላለች።

እንደ ታሪኩ ከሆነ በሳጥን ውስጥ ለሶስት ቀናት እና ሶስት ሌሊቶች አሳልፋለች። በዚህም 700 ማይል (1127 ኪሎሜትር) ርቀት ተጉዛለች።

ማሪያ ከደረሰባት መከራ በኋላ የጠላት ወኪል በሚል ተጠርጥራ ወደ እስር ቤት ገባች። በእስር ቤትም 24 ቀናትን አሳለፈች።

በሌላ በኩል መኮንኑ ፍቅረኛዋ ወታደራዊ ትዕዛዝን ባለማክበርና እና በሌሎች ክሶች ለስድስት ሳምንታት ያህል ታሰረ። በኋላም በጠንካራ ተግሳፅ እንዲወጣ ተደረገ።

ከእስር ከተለቀቀ ከአራት ቀናት በኋላ ማሪያ እና መኮንኑ ፍቅረኛዋ በአውሮፓውያኑ ሀምሌ 12፣ 1942 በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጋቡ።

"ከአስመራ ለመውጣት ባልወስን ኖሮ ባለቤቴን ለማግባት ዕድል አላገኝም ነበር" ስትል ማሪያ ተናግራለች።

ከመከራ በኋላ ህይወት

ከዚያ ለፍቅር ሲባል ከተከፈለ አስፈሪና አስገራሚ ጉዞ በኋላ ማሪያና ባለቤቷ ከልጆቻቸው ጋር በእንግሊዝ አስደሳች ህይወት መርተዋል።

ይሁን እንጂ በሚያሳዝን ሁኔታ የዚህ አስደናቂ የፍቅር ባለታሪኮች ከጋብቻ በኋላ ስለነበራቸው ህይወት ብዙ መረጃ የለም። የማሪያ እናት ወይዘሮ ስላስ ማሪያን በእንግሊዝ እንደጎበኟት የሚያሳይም ምንም መረጃ አልተገኘም።

የታሪኩ ፀሃፊ ባደረገው ጥናት መሰረት ማሪያ መኮንን ፍቅረኛዋን ካገባች በኋላ ስሟ ሶልስቢ ስፑነር በሚል ተቀይሯል።

ማሪያ የሞተችው በባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ሲሆን እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው ሃምሻየር ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓቷ ተፈጽሟል።

ታዋቂው የበሽታ አመጣጥ (ፓቶሎጂስት) ተመራማሪና የማሪያ ታናሽ ወንድም የሆኑት ዶክተር ሴሳሬ ማኔቴ በእርጅና ዘመናቸው ወደ ኤርትራ ተመልሰው የነበረ ሲሆን በቃለ ምልልሳቸው ላይ ስለ እህታቸው ምንም አላሉም።

የማሪያን እናት ወይዘሮ ስላስን ጠንቅቀው የሚያውቁ ዘመዶች እና ጓደኞችም በቀጥታ ቃላቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል፤ ነገር ግን ማሪያ ለፍቅረኛዋና ለፍቅሯ ስትል ከቤት ወጥታ መኮብለሏን ያምናሉ።

ማሪያ አስመራን እንዳልጎበኘች እና እስከ ህልፈቷ ድረስ እውነተኛ ማንነቷን መደበቅ መፈለጓን በተመለከተ በተጨባጭ የተሰበሰቡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ማሪያ ታዋቂውና ታሪካዊው ሳጥን ወደ እንግሊዝ እንደመጣ በወቅቱ ተናግራ ነበር።