ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ሙቀት መጨመር በቡና፣ በአቮካዶና በሌሎች ሰብሎች ላይ ምን ያስከትል ይሆን?
ለቡና፣ ለአቮካዶና ለኦቾሎኒ ምርቶች ልማት ተስማሚ የሆኑት አገራት የዓለም ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚለወጡ አዲስ ጥናት አመለከተ።
በዓለም ውስጥ ዋነኛ ቡና አብቃይ የሚባሉት ብራዚል፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቬትናም እና ኮሎምቢያን የመሳሳሉ አገራት በአውሮፓውያኑ 2050 ለምርቱ ያላቸው ተስማሚነት በአስደንጋጭ ሁኔታ 50 በመቶ ይቀንሳል።
ለኦቾሎኒና ለአቮካዶ የሚሆኑ ተስማሚ ስፍራዎች በዓለማችን ይጨምራሉ፤ ነገር ግን አብዛኖቹ አሁን ካሉት የምርት ቦታዎች በጣም የራቁ ይሆናል።
ይህንን ምርምር ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚሉት አርሶ አደሮች መጪውን ጊዜ መላመድ እንዲችሉ ከፍተኛ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።
ቡና በዓለማችን ጠቃሚ ከሚባሉት ተክሎች አንዱ ነው፣ ዋነኛ መጠጥ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩና አናሳ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች መተዳደሪያ ከሆኑት ሰብሎች አንዱ ነው።
በበለጸጉ አገራት እያደገ ለመጣው የሸማቾች ምርጫ ምስጋና ይግባውና ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ የአቮካዶ እና የኦቾሎኒ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት በቡና ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚገባ የተጠናና የተሰነደ ቢሆንም፣ የሙቀት መጠን መጨመር በአቮካዶ እንዲሁም በኦቾሎኒ ላይ ምን ያህል ተፅእኖ እንደሚያሳድር ብዙም መረጃ የለም።
በዚህ ጥናት ተማራማሪዎቹ የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር እና የእርጥበት መጠን መለዋወጥ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ በሦስቱ ምርቶች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተመልክተዋል። ተመራማሪዎቹ በዚህ ጥናታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ መሬት እና የአፈር ባህርያት መረጃ አካተዋል።
ቡና በከፍተኛ ሙቀት የሚበላሽ ሰብል ነው። ቡና አብቃይ በሆኑት አገራት በዋናነት የሚመረተው አረቢካ የተባለው የቡና ዝርያ ሲሆን ይህንን ሰብል ለማብቀል ተስማሚ የመሆናቸው መጠን በጣም ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ በግማሽ ይቀንሳል ይላል ሪፖርቱ።
በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች የከፋ ተፅእኖ የሚታይ ይሆናል። ለምሳሌ በብራዚል በጣም ዝቅተኛ በሆነ የሙቀት መጠን እንኳን ለቡና ተስማሚ የሆኑ አካባቢዎች በ76 በመቶ ይቀንሳል። በኮሎምቢያም እንዲሁ ተስማማሚነቱ በ63 በመቶ ይቀንሳል።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አርጀንቲና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና እና ኒውዚላንድን ጨምሮ ሌሎች አገራት ይበልጥ ተስማሚ ይሆናሉ።
ነገር ግን እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ይህ ማለት ለመጪው ጊዜ ለሰብሎቹ ተስማሚ የሆኑት አዳዲስ ስፍራዎች በአሁኑ ወቅት ያሉትን አብቃይ አካባቢዎች በቀላሉ መተካት ይችላሉ ማለት አይደለም።
"ቁልፉ መልዕክት በዋነኝነት የእነዚህ ሰብሎች አብቃይና አምራች የሆኑ አካባቢዎች የግብርና ሥርዓታቸውን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ማላመድ አለባቸው" በማለት የምርመሩ መሪ የሆኑትና በዙሪክ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ሮማን ግሩተር ይናገራሉ።
"ቡና በአሁኑ ወቅት በአዳዲስ አካባቢዎች መብቀል ጀምሮ ከሆነ ወይም አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርጎበት የሚበቅል ከሆነ ሁኔታዎች ቀለል ሊሉ ይችላሉ ወይም ሰብሎቹ በሰፊው ሊበቅሉ ይችላሉ። ይህ ማለት ግን በመጪዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ ፍጹም ተስማሚ አብቃይ አካባቢዎችን እናገኛለን ማለት አይደለም" ይላሉ።
ያለው ሁኔታ ለኦቾሎኒ ምርት ከቡና የተለየ ነው። በአጠቃላይ ለኦቾሎኒ ሰብል ልማት በከፍተኛ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ስፍራዎች 17 በመቶ ይጨምራሉ።
ነገር ግን ኦቾሎኒን በዋነኝነት የሚያመርቱና በገቢነትም ለሚተማመኑበት ዜናው ጥሩ አይደለም። ሕንድ በጎላ መልኩ ተስማሚነቷን ታጣለች። ቤኒን ደግሞ በጣም ዝቅተኛ በሆነው የሙቀት መጨመር ምክንያት ተስማሚ የሆነውን ግማሽ ቦታዋን ታጣለች።
ከቡናና ኦቾሎኒ በተለየ መልኩ በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ ፍሬውን በሚያመርቱት አገራት ውስጥ ለአቮካዶ ምርት ሁኔታዎች የተወሳሰቡ ናቸው።
በዓለም ላይ ዋነኛ የአቮካዶ አምራች የሆነችው ሜክሲኮ ተስማሚ የሆነው መሬቷ 80 በመቶ በሚደርስ መጠን ይጨምራል። ነገር ግን ሌላኛዋ ዋነኛ የኦቮካዶ አብቃይ የሆነችው ፔሩ በተመሳሳይ የአየር ንብረት ውስጥ ብትሆንም ግማሽ ያህል ተስማሚነቷን ታጣለች።
የአየር ሙቀት መጨመር እና የዝናብ ሁኔታ ለውጦች አንዳንድ አካባቢዎችን ይበልጥ ተስማሚ ሊያደርጋቸው ቢችልም፣ ተመራማሪዎቹ እነዚህን ሰብሎችን በአዳዲስ አካባቢዎች ለማብቀል በሚደረገው ሂደት ብዙ ደኖች ወደ እርሻ መሬትነት ሊለወጡ ወይም በአረሞች ሊሸፈኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።
"እነዚህን ሰብሎችን ለማብቀል በበለጠ ተስማሚ ሊሆኑ የሚችሉ ስፍራዎች ላይ እንደ ደን መጨፍጨፍ ያሉ አሉታዊ የአካባቢ ተፅእኖዎች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው" ይላሉ ሮማን ግሩተር።
"በእነዚህ ሁሉ ለውጦች የአካባቢው ባለድርሻ አካላት፣ ማኅበረሰቦች በእነዚህ ተለዋዋጭ ሂደቶች ውስጥ መሳተፍ አለባቸው። እውነተኛ በሆነ መንገድ አሳታፊ መሆን አለበት" ይላሉ።
የሲሲሊ ተሞክሮ
ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በሲሲሊ በ1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን መጨመር ያጋጠመ ሲሆን ይህም ሁኔታ አርሶ አደሮች ሞቃታማ በሆኑ ስፍራዎች ወደሚበቅሉ ሰብሎች እንዲዞሩ አድርጓቸዋል።
ከእነዚህም መካከል አንዱ አንድሪያ ፓሳኒሲ ሲሆን በኤትራ ተራራ አቅራቢያ አቮካዶ ያመርታል። ይህም ለእሱም ሆነ በአካባቢው ላሉ አምራቾች ስኬት ሆኖላቸዋል።
ይሁን እንጂ የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ሲሄድ፣ የሰብሉ የመብቀል ሁኔታም በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።
"እውነተኛው የአየር ንብረት ለውጥ በወቅቶች ላይ ይታያል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"በኅዳር እና በታኅሣሥ ቀዝቃዛ ነበር፣ አሁን ጥር ወይም የካቲት ላይ በጣም ሞቃት በመሆኑ ለአቮካዶ ጥሩ አይደለም" ይላል።
ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንዲሁም የድርቅ ሁኔታ መጨመር ለአርሶ አደሮች ፈታኝ ሁኔታን ይፈጥራል።
"ለአቮካዶ የማይመች መሬት ላይ ብትተክሉ ከንቱ ልፋት ነው" ይላል አንድሪያ።
"ጥሩ መሬት ስላለን መትከል እንቀጥላለን፣ ነገር ግን ብዙ ውጤታማ አንሆንም፣ ምርትም አይኖረንም" በማለት ያስረዳል።
የሙቀት መጠን መለዋወጥ በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ ሰብል አብቃዮች መጥፎ ዜና ቢመስልም፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ አርሶ አደሮች ሊወስዷቸው የሚችሏቸው አንዳንድ ጥሩ እርምጃዎች አሉ።
"በአሁኑ ጊዜ አቮካዶ በሚበቅልባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የአቮካዶን ዘረመል መለዋወጥ ሊረዳ ይችላል" በማለት በአዲሱ ጥናት ያልተሳተፉት የኮሎምቢያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ጆአኩዊን ጊለርሞ ራሚሬዝ ጊል ይናገራሉ።
"አቮካዶ የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አመጣጥ ያላቸው ሦስት ዝርያ አለው። ይህም ሁኔታ ከተለያዩ የአየር ሁኔታዎች ጋር ለመላመድ ያመቸዋል" ይላሉ።
"በተጨማሪም የአካባቢ መላመድ እና አበረታች ንጥረ ነገሮች እና ናኖ ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ አማራጮችን በመጠቀም የአስከፊ የአየር ሁኔታን መቋቋም የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይቻላል" በማለት ያስረዳሉ።