ቴክኖሎጂ፡ የአምስት ዓመቷ የኮዲንግ ተማሪ ሳሌም እና የ 'የኔታ' መምህሯ ናታን

ጣቶቿ እንኳንስ የኮምፒውተር ቀመር ለማስላት፤ የኮምፒውተር ማውዝ በቅጡ ለመጨበጥም አልጠነከሩም።

ሳሌም ብሩክ ትባላለች። ገና አምስት ዓመቷ ነው።

እናቷ ኮከብ እና አባቷ ብሩክ የኮዲንግ ትምህርት ቤት ሲልኳት "ትንሽ ነች፣ እጇም ትንሽ ነው። ማውዙን እንዴት ትይዛለች? ኪቦርዱን እንዴት ትቆጣጠራለች?" እያሉ ነበር።

ሁሉም ሰው ኮዲንግ መማር ይችላል የሚለው መምህሯ ናታን ዳምጠው የኔታ በር ላይ ተቀበላት።

ሳሌም ወላጆቿንም መምህሯንም ባስደመመ ሁኔታ መሠረታዊ የኮዲንግ ትምህርትን ልቅም አድርጋ ቀሰመች።

2000 የኮዲንግ መስመሮች ጽፋ፣ ለ50 የኮዲንግ ፈተናዎች መልስ ሰጥታ ከየኔታ ኮድ ማዕከል ተመረቀች።

የየኔታ ኮድ መሥራችና የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ መምህር ናታን ካስተማራቸው ልጆች በዕድሜ ትንሿ ሳሌም ናት።

ለመሆኑ ሳሌም ስለ ኮዲንግ ምን ታስባለች? ስንል እናቷ ኮከብ ጋር ደወልን። ለአምስት ዓመት ልጅ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ቀላል ባይሆንም ሳሌምን በእናቷ ፈቃድ እንዲህ አዋርተናታል።

ሳሌም ደኅና ነሽ?

ደኅና

ጋዜጠኛ ነኝ። ጥያቄ ልጠይቅሽ?

እሺ

ኮዲንግ ተምረሻል አይደል?

አዎ

ምን አስተማሩሽ?

በአሮ ተጠቅመሽ ወደ ኖርዝ ወደ ኢስት ወደ ዌስት መሄድ ነው የተማርኩት. . . ወደ ቀኝ መሄድ ካስፈለገ ቀኝ እናስቀምጣለን፣ ወደ ግራ መሄድ ካስፈለገ ግራ እንገጥማለን።

ኮዲንግ ትወጃለሽ?

አዎ! ስክራችም እወዳለሁ።

እስኪ ስክራች ምን እንደሆነ አስረጂኝ?

ከኮዲንግ ጋር የሚገናኝ ነው። መንቀሳቀስ ከፈለግሽ ጎ የሚል አለ። እሱን ስትነኪው ይሄዳል። ከሄደ በኋላ ማቆም ስትፈልጊ ቀይ አለ። ቀዩን ስትነኪው ይቆማል. . . ስለ አይስ ኤጅ ደግሞ ልንገርሽ። አይስ ኤጅ የበረዶ መሬት ነው። ውሃ ውስጥ ከገባሽ ትፎርሻለሽ። ትልቁ የበረዶ መሬት ላይ ከወጣሽ ታሸንፊያለሽ። እና ውሃ ውስጥ ላለማረፍ መሬቱ ላይ ዘለሽ ትወጫለሽ።

ከዚህ በኋላም ኮዲንግ መማር መቀጠል ትፈልጊያለሽ?

እእእ. . . አዎ! [ረዥም ሳቅ]

ስታድጊ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?

ሳድግ ሳይንቲስትም ሙዚቃ የሚዘምርም መሆን ነው የምፈልገው። [ቤት ውስጥ] መዝሙር እየዘመርኩ በኮምፒውተር ድምጼን እቀዳለሁ።

እሺ ሳሌም፤ ጎበዝ ነሽ! በርቺ!

አመሰግናለሁ፤ ቻውውው. . .

ሳሌም ስለ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ የምታወራው ለምንድን ነው? አቅጣጫ እና ኮዲንግ ምን አገናኛቸው? አይስ ኤጅ የኮምፒውተር ጌም ከኮዲንግ ጋር ምን አስተሳሰረው? ስንል መምህር ናታንን ጠይቀናል።

ናታን ኮዲንግ ወይም ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግን ከሥር ከመሠረቱ ለማስረዳት ወደ መጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ይወስደናል።

በመጀመሪያው የትምህርት ቀን፣ በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ናታን ልጆችን "ጌም ትወዳላችሁ?" ብሎ ይጠይቃል።

ከእናት ከአባቶቻቸው ስልክ በቀላሉ የማይላቀቁ የዛሬው ትውልድ ልጆች መልሳቸው "በጣም ነው ጌም የምንወደው!" ይሆናል።

እንግዲያውስ ጌም እንዴት እንደሚሠራ አስተምራችኋለሁ፤ ይልና ናታን ትምህርቱን ይጀምራል።

ይህንን የመጀመሪያውን ክፍለ ጊዜ ናታን በጣም ይወደዋል። ያስደስተዋልም።

በርካታ ልጆች ጌም መጫወት እንዲሁም ካርቱን ፊልም ማየት ስለሚያዘወትሩ በሚወዱት ነገር በኩል ኮዲንግ ያስተምራቸዋል።

ገና ማንበብ ያልለመዱ ተማሪዎችን የሚያስተምረው በቀለምና በቅርጽ ነው።

ለምሳሌ 'አንግሪ በርድስ' የተባለውን ጌም እንውሰድ። እዚህ ጌም ላይ ካሉት ገጸ ባህሪዎች አንዱ ይወሰዳል።

ለአራቱ አቅጣጫዎች ቀለም ይሰጣል። አፕል ከአራቱ አቅጣጫዎች በቅርብ ርቀት ይቀመጣል።

ከዚያ የጌሙ ገጸ ባህሪ አፕሉ ጋር ለመድረስ ከየት አቅጣጫ ወደ የት መሄድ አለበት? ተብሎ ልጆች ይጠየቃሉ።

ልጆች በአቅጣጫ ጠቋሚ ተጉዘው ገጸ ባህሪውን አፕሉ ጋር ሲያደርሱ የመጀመሪያውን ትምህርት አገኙ ማለት ነው።

"በዚህ መንገድ ሲኩዌንሲንግ የሚባለውን የፕሮግራሚንግ ጽንሰ ሐሳብ እናስተምራቸዋለን። ትምህርቱ ሲያልቅ ልጆቹ ጌም ሲጫወቱ የቆዩ ነው የሚመስላቸው። ጌሚፋይድ ለርኒንግ [በጨዋታ መልክ የተዘጋጀ ትምህርት] ይባላል" ይላል ናታን።

ከአቅጣጫ ጠቋሚ ቀስቶች ጀርባ ያለው የፕሮግራሚንግ ቋንቋ ነው። ተማሪዎቹ ማንበብ ሲማሩ ቅርጾቹ በጽሑፍ ይቀየራሉ።

ጽሑፎቹ መመሪያዎች ናቸው። መመሪያዎቹን ተከትሎ ለአንድ የኮምፒውተር ችግር መፍትሔ መስጠት ይቻላል።

ኮዲንግ ማለት በኮምፒውተር ቋንቋ ተጠቅሞ የኮምፒውተርን ችግር መፍታት ነው።

ኮዲንግ ለልጆች ምን ይፈይዳል?

የኔታ ካስተማራቸው 1200 ተማሪዎች ሁለቱ ሳሌም እና የሰባት ዓመት ወንድሟ አቤም ናቸው።

ኮከብ እና ባለቤቷ ልጆቻቸውን ኮዲንግ ለማስተማር የወሰኑት አንድም ቴክኖሎጂ-ተኮር ዘመኑን ከግምት በማስገባት፣ ሌላው ደግሞ ልጆቹን አዲስ እውቀት ለማስጨበጥ፣ እንዲሁም ልጆቹን ለማዝናናት ነው።

ክረምት በመጣ ቁጥር እግር ኳስ፣ ቴኳንዶ እና ሌላም ያስተምሯቸዋል።

የኮከብ ባለቤት የአይቲ ባለሙያ ነው። ኮዲንግ ለልጆች የሚል ነገር ሲሰሙ እስኪ ይሞክሩት ብለው ላኳቸው።

"እንዲማሩ የወሰነው ሳሌም ለኮዲንግ የተለየ ዝንባሌ አሳይታ አልነበረም። አዝናኝ በሆነ መንገድ አዲስ ነገር እንዲያውቁ ብለን ነው" ትላለች ኮከብ።

ሳሌም እና አቤም ትምህርቱን በፍጥነት እንደተቀበሉ ታስታውሳለች። እንዲያውም 6 ሰዓት ደርሶ ከትምህርት ቤት ሊወስዷቸው ሲሄዱ ልጆቹ ለመውጣት ያንገራግሩ ነበር።

ካለንበት ቴክኖሎጂ-ተኮር ዓለም እኩል ለመራመድ ኮዲንግ መማር ግዴታ እየሆነ መጥቷል።

ኮከብ ልጆቿን ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ለማስተማር ዩኒቨርስቲ እስኪደርሱ መጠበቅ አትሻም።

"ከወዲሁ ልጆችን ወደዚያ መስመር ማስገባት ይጠቅማል። [ቴክኖሎጂ] በእኛ ጊዜ እንደነበረው ሩቅ አይደለም። ልጆችም እንዲቀላቸው፣ እንዲያውቁትና እንዳይፈሩት ማድረግ ጥሩ ነው" ትላለች።

ባደጉት አገራት ኮዲንግ መቻል ሥራ ለመቀጠር እንደ መስፈርት እንደሚወሰድ ናታን ይናገራል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቁ ናታን፤ ዩኒቨርስቲ እስከሚገባ ድረስ ስለ ፕሮግራሚንግ አያውቅም ነበር።

ከራሱ ተሞክሮ ተነስቶ ነው ልጆችን በጊዜ ኮዲንግ ማስተማር የጀመረው። ልጆችን ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ለማስተማር ቢ-ብሎኪ የተባለ መተግበሪያም ፈጥሯል።

"ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግን በልጅነት ካስተማርናቸው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲሄዱ ኮዲንግ ይቀላቸዋል።"

ኮዲንግ እና የአእምሮ እድገት

የኮዲንግ መሠረታዊ ሐሳብ የኮምፒውተር ችግርን መፍታት ነው። ችግር የመፍታት ክህሎቱ ከኮምፒውተር ባለፈ በዕለት ከዕለት ሕይወትም ይተገበራል።

ልጆችን ኮዲንግ ማስተማር አእምሯቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደማሠራት ነው።

የሒሳብና የሳይንስ ችሎታቸው ይጎለብታል። ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ መቃኘትን ይማራሉ።

ኮከብ እንደምትለው፤ የልጆቿ አእምሮ የተለየ ምልከታ እንዲኖረው ነው ኮዲንግ ያስተማረቻቸው። ጎን ለጎን እንዲዝናኑም ጭምር።

ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ አእምሮ ችግር የመፍታት ክህሎትን ቢያዳብርም፤ በልጅነት ኮዲንግ መማር ሂደቱን እንደሚያፈጥነው ናታን ይናገራል።

ሳሌም እና አቤም በቤታቸው ኮምፒውተር ላይ በተጫኑ መተግበሪያዎች ኮዲንግ አዘውትረው ይለማመዳሉ።

"የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ትልቁ ዋጋው የአእምሮ እድገት ነው። ኮዲንግ የሚማሩ ልጆች ፈጣን ይሆናሉ፤ ቶሎ መፍትሔ ያመጣሉ" ይላል ናታን።

ከፍ ሲሉ ድረ ገጽ ወይም መተግበሪያ ወደመፍጠር ሊሻገሩም ይችላሉ።

ናታን ከሥራ ውጪ ባለ ሕይወቱም፤ አንድን ችግር በአንድ በኩል መፍታት ካልተቻለ ሌላ መንገድ አይጠፋም የሚል አቋም ያራምዳል።

"በፊት የምሠራበት ቦታ የተገለበጠ የባሕር ዳርቻ ሥዕል ነበር። ውሃው ከላይ፣ ጸሐይ ከታች ይታያሉ። ሥዕሉ አንድን ነገር ከተያየ አቅጣጫ እንዳይ ያስታውሰኛል" ሲል በምሳሌ ያሰረዳል።

ኮዲንግ ተሰጥኦ ነው?

ማንኛውም ሰው ወደ ኮዲንግ መግባት እንደሚችል ናታን ይናገራል።

ዘፋኝ በድምጹ፣ ሯጭ በሜዳልያው እንደሚለካው፤ በኮዲንግ ጎበዝ የሚባል ሰው እንዴት ይለካል? ስንል መምህሩን ጠይቀናል።

የኮምፒውተር ችግርን በፍጥነት መፍትሔ የሚሰጥ ወይም በአጭር ጊዜ ለብዙ የኮምፒውተር ችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ የሚያበጅ በኮዲንግ ይደነቃል።

ናታን ተማሪዎቹን በዕድሜ እና በአቅማቸው ከፋፍሎ ነው የሚያስተምረው።

ተማሪዎች ከተማሪዎች ጋር ሳይወዳደሩ፣ በፈጣን ተማሪ ልክ የተቀሩት ተማሪዎች ሳይመዘኑ ሁሉም በአቅሙ ችግር እንዲፈታ ጊዜ ይሰጣል።

ሳሌም በዕድሜ ትንሿ ተማሪው በመሆኗ በልዩ ያስታውሳታል።

"ከእሷና ከወንድሟ ጋር በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍነው። ሳሌም የአቀባበል ሁኔታዋ፣ ነገሮችን ቶሎ የምትረዳበት መንገድ እና ቶሎ ተረድታ መፍትሔ መፈለጓ ለየት ያደርጋታል" ይላል።

ከሳሌም በኋላ ሌሎችም ትንንሽ ልጆች ወደ የኔታ እየሄዱ ነው።

ሳሌም የተለየ የኮዲንግ ተሰጥኦ አላት? ያልናት ኮከብ "ይህንን ለማወቅ ትምህርቱን መቀጠል አለባት። ጊዜ ሰጥቶ መከታተልም ያስፈልጋል" ስትል መልሳለች።

ልጅ በመሆኗ ኮዲንግ አዲስ ነገር ሆኖባት ትውደደው፣ ወይም እጣ ክፍሏ ይሁን ለማወቅ ጊዜው ገና ነው ብላ ታምናለች።

ወላጆች ባላቸው አቅም እና ጊዜ ልጆቻቸውን በተለያዩ ክንውኖች እንዲያሳትፉ ምክሯን ጣል ሳታደርግ ግን አላለፈችም።

ኮምፒውተር ከመጠቀም ወደ መሥራት

ደምበል ሲቲ ሴንተር የሚገኘው የኔታ 4 ዓመት አስቆጥሯል። በትምህርት ቤቱና በቢ-ብሎኪ የሞባይል መተግበሪያ 20 ሺህ የሚጠጉ ታዳጊዎች ተምረዋል።

አምስት ዓመት አካባቢ ያሉ ልጆች ቅድመ ንባብ በሚባል ደረጃ በቅርጽና ቀለም ይማራሉ።

ከፍ ሲሉ በጽሑፍ ትምህርቱ ይሰጣቸዋል።

ከአንድ ክፍል ወደ ቀጣዩ ለማለፍ 3 ወር ያስፈልጋል። ለአጭር ጊዜ ወይም በዘላቂነት መማርም ይቻላል።

ለሦስት ወር ትምህርት ከ5 ሺህ እስከ 7 ሺህ ብር ይከፈላል። የተወሰኑ መክፈል የማይችሉ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጣቸውና ሲያጠናቅቁ እዚያው በማስተማር ያገለግላሉ።

ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስገባት ከመወሰናቸው በፊት ለአንድ ሰዓት የሙከራ ትምህርት እንደሚሰጥ ናታን ይናገራል።

በሙከራው ከሚሳተፉ ከ90 በመቶ በላይ ልጆች ይመዘገባሉ። 85 በመቶ የሚሆኑት 3 ወር ሲማሩ፤ 70 በመቶ ወደሚቀጥለው ክፍል ይሻገራሉ።

የኔታ በግል ትምህርት ቤቶችና ከመንግሥት ጋር ሆኖ በወጣት ማዕከሎች ቅርንጫፍ የመክፈት ጅማሮ ላይ እንደሆነ መሥራቹ ይናገራል።

የኔታ የተማሩ ልጆች የት ደረሱ? ያልነው ናታን "ዌብ ሳይት ለጓደኞቹና ለራሱም የሠራ የ13 ዓመት ልጅ አለ። ፓክማን እና ሱፐርማርዮን የሚመስሉ ጌሞች የሠሩም አሉ" ሲል መልሷል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ የኔታ ሲወስዱ መጀመሪያ የሚሉት "ሁሌ ጌም ትጫወታለች" "ጌም ብቻ ከሚጫወት ለምን የራሱን አይሠራም?" "ለምን በታብሌቱ ከምትጫወት አትማርም?" ወዘተ. . . ነው።

የ1980ዎቹ ትውልድ በልጅነቱ ቋንቋ፣ ዋና፣ ውሹ ሲማር እናስታውሳለን። ዛሬ ግን ወላጅ ልጁን ከኮምፒውተር ተጠቃሚነት ወደ ኮምፒውተር ሠሪነት ማሳደግ ይመኛል።

የናታን ግብም ተመሳሳይ ነው።

አጭር የትኩረት መስኮት ብቻ የሚሰጡ ልጆችን በአንዴ ጌም ሠሪ ማድረግ ባይቻልም ጠንካራ መሠረት በመጣል ያምናል።

"ልጆችን ማስተማር ፈታኝ ነው። በሚሰጡኝ ውስን ትኩረት የቻልኩትን ለማስተማር እሞክራለሁ" ይላል።

በዕድሜ ከፍ ያሉትን ማስተማርም ቀላል አይደለም።

"ልጆች ሲሆኑ ነጭ ወረቀት ላይ እንደመጻፍ ነው። ከፍ ያሉት ለትምህርቱ ትኩረት መስጠት ቢችሉም አንዳንድ ቀድሞ የሚያውቋቸውን ነገሮች ሰርዞ በአዲስ እውቀት መተካት ሌላ ፈተና ነው" ሲል ያስረዳል።

ኮምፒውተራቸው ያቀረበላቸው መተግበሪያዎች ላይ ጊዜ ከማጥፋት፤ ለራሳቸው ፈጠራ ዘለግ ያለ ሰዓት የሚሰጡ ልጆች በማፍራታቸው ይኮራል።

ቤተሰብም "ለልጆቻችን መሠረት ሰጣችሁልን" እያለ ያመሰግናቸዋል።

ኮከብ፤ ሳሌም ራሷን ችላ ኮምፒውተር ላይ የፈለገችውን ስታደርግ ማየቷን "ትልቅ ስኬት" ትለዋለች።

ማን ያውቃል? ቀጣዩዋ ትምኒት ገብሩ ወይም ቀጣዩ ቢል ጌትስ የሚፈጠሩት ከዚህ ይሆናል. . .