ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት ኦሚክሮን የሚያስከትለው ህመም መለስተኛ ነው መባል የለበትም አለ
የዓለም ጤና ድርጅት የኦሚክሮን ዝርያን መለስተኛ ሕመም የሚያስከትል በሚል መገለጹ እንዳሳሰበው እና በዓለም ዙሪያ ለሰዎች ሕልፈት ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ማስጠንቀቂያ አወጣ።
በቅርቡ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኦሚክሮን የተያዙ ሰዎች በቀደሙት የኮቪድ-19 ዝርያዎች ከተያዙ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር በጠና የመታመም እድላቸው ያነሰ ነው።
ነገር ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን እና ይህም የጤና ሥርዓቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ዕለት አሜሪካ በ24 ሰዓት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን በመለየት ከፍተተኛውን ቁጥር መዝግባለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት የጤና ተቋም ባወጠው መረጃ ባሳለፍነው ሳምንት በመላው ዓለም ያለው በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ በ71 በመቶ ሲጨምር በአሜሪካ ከ100 በመቶ በላይ ጨምሯል። በመላው ዓለም በጠና ከታመሙት ውስጥ 90 በመቶው ያልተከተቡ መሆናቸውንም አመልክቷል።
"ኦሚክሮን ከዴልታ ጋር ሲነፃፀር፤ በተለይም ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ ያን ያህን የከፋ ባይሆንም መለስተኛ ተብሎ መመደብ አለበት ማለት አይደለም" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
"ልክ እንደ ቀደሙት የቫይረሱ ዝርያዎች ሁሉ ኦሚክሮንም ሰዎች በጠና ታመው ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ እና ሕይወታቸው እንዲያልፍ እያደረገ ነው።
እንዲያውም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ልክ እንደ ሱናሚ ግዙፍ እና ፈጣን በመሆኑ በዓለም ዙሪያ የጤና ሥርዓቶችን አቅም ከልክ በላይ አስጨንቋል" ሲሉም ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል።
በመላው ዓለም በከፍተኛ መጠን በመሰራጨት ላይ የሚገኘው ቫይረሱ ሐሙስ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም 179 ሺህ 756 ሰዎችን መያዙ ሲረጋገጥ 231 ከቫይረሱ ጋር የተዛመደ ሞትም አስከትሏል።
በርካታ ሆስፒታሎች በሠራተኞች በሥራ ገበታው ላይ ባለመገኘት እና በኮቪድ-19 ምክንያት እየጨመረ በመጣው ጫና ሳቢያ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።
የፈረንሣይ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኦሊቪየር ቬራን በዚህ ሳምንት እንደተናገሩት ይህ የፈረንጆቹ የጥር ወር ለሆስፒታሎች ከባድ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ዴልታ በጽኑ ሕሙማን ከፍል ላይ ጫና እያሳደረ ባለበት ወቅት የኦሚክሮን ህመምተኞች በሆስፒታሎች ውስጥ ለሌሎች ህሙማን የተተዉ አልጋዎችን እየያዙ መሆኑን አክለዋል።
ፈረንሳይ ሐሙስ ዕለት 261 ሺህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር መዝግባለች።
የሰርቢያው ፕሬዝዳንት አሌክሳንዳር ቩቺች የሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው ብለዋል።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ሐሙስ ዕለት ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።