ኮቪድ-19፡ የቻይናዋ ዢያን ከተማ ነዋሪዎች በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ንብረታቸውን በምግብ እየቀየሩ ነው

በቻይና ዢያን ከተማ በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት የምግብ እጥረት ስጋት በመፈጠሩ ነዋሪዎች ንብረታቸውን በምግብ እየቀየሩ ነው።

በማኅበራዊ ድር አምባ በተለቀቁ መረጃዎች መሠረት የአካባቢው ነዋሪዎች ሲጋራዎችን እና የቴክኖሎጂ መገልገያዎችን በምግብ ሲቀይሩ ታይተዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ወደ 13 ሚሊዮን የሚጠጉ የከተማዋ ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቀመጡም ተገደዋል።

እርምጃው የተወሰደው ከቻይናውያን አዲስ ዓመት እና በሚቀጥለው ወር በቤይጂንግ ከሚካሄደው የክረምት ኦሊምፒክ ቀደም ብሎ ነው።

ዩዡ ከተማ ሦስት ምልክት ያላሳዩ ሰዎች በኮቪድ መያዛቸውን ተከትሎ ነው በአንድ ምሽት በከተማዋ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው።

1.1 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ዩዡ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዋን እና የመዝናኛ ሥፍራዎቿን የዘጋች ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ተሽከርካሪዎች ከጉዞ አግዳለች።

ወረርሽኙን በመከላከል ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞች ብቻ መንቀሳቀስ ሲፈቀድላቸው ከወሳኝ የምግብ መሸጫ ሱቆች ስተቀር ሌሎቹ ተዘግተዋል።

አገሪቱ ከቫይረሱ ጋር አብሮ ለመኖር ከመሞከር ይልቅ ማጥፋት በሚል "የዜሮ ኮቪድ" ስትራቴጂን ለወራት ተግብራለች።

የዢያን ባለሥልጣናት ለነዋሪዎች ነጻ ምግብ ቢያቀርቡም ብዙ ቅሬታዎች በማኅበራዊ ድር አምባ ላይ ተሰምተዋል። አንዳንድ ነዋሪዎች ያላቸው ምግብ እያለቀ ወይም እስካሁን እርዳታ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

ዌይቦ በተሰኘው የአገሪቱ ማኅበራዊ ድር አምባ የተሰራጩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ነዋሪዎች ሲጋራን በጎመን፣ የዕቃ ማጠቢያ ፈሳሽን በፖም እና የንፅህና መጠበቂያዎችን በአነስተኛ አትክልት ሲቀይሩ አሳይተዋል።

ዋንግ የተባለ ነዋሪ ለሬዲዮ ፍሪ ኤዥያ እንደተናገረው "ከአሁን በኋላ የሚበሉት በቂ ምግብ ስለሌላቸው በተመሳሳይ ሕንጻ ውስጥ ያላቸውን እርስ በርስ እየተለዋወጡ ነው።"

የዜና ማሰራጫው አክሎም ሌላ ግለሰብ ዘመናዊ ስልኩን እና ታብሌቶቹን በሩዝ ለመቀየር ፈልጎ እንደነበር ዘግቧል።

"አማራጭ የሌላቸው ዜጎች ዕቃን በዕቃ የመገበያያ ዘመን ላይ በመድረሳቸው ድንቹን በጆሮ መጥረጊያ ጥጥ ይለወጣሉ" ሲል አንድ የዌይቦ ተጠቃሚ ገልጿል። ሌላው ደግሞ [ሁኔታውን] "ወደ ጥንታዊው ማኅበረሰብ መመለስ" ሲል ገልጾታል።

አንዳንዶቹ የበለጠ ተስፈኞች የሆኑ ሲሆን ጎረቤቶቻቸውን ያላቸውን በማካፈል ምን ያህል "ልባቸውን እንደነኩ" ገልጸዋል።

ዢያን በአሁኑ ወቅት የቻይና የኮቪድ ወረርሽኝ ማዕከል የሆነች ሲሆን የአካባቢው ባለሥልጣናት በወሰዷቸው ከባድ እርምጃዎች ምክንያት ከፍተኛ ትችት እያስተናገዱ ነው።

ነዋሪዎች ሰኞ ዕለት በበይነ መረብ በተለቀቀው ያልተረጋገጠ መረጃም ተደናግጠዋል። አንድ የዢያን ነዋሪ አባታቸው በልብ ህመም ህይወቱ ማለፉን እና በከተማው ባለው ኮቪድ ምክንያት ከሆስፒታል መመለሳቸውን ተናግሯል። በዚህ ዙሪያ ሆስፒታሉ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።