ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በረራ ላይ ሳለች ኮቪድ-19 የተገኘባት ተጓዥ ለሰዓታት በመጸዳጃ ቤት ራሷን አገለለች
በረራ ላይ ሳለች ኮቪድ-19 እንዳለባት ያወቀችው አሜሪካዊት መምህርት በአውሮፕላኑ መጸዳጃ ቤት ራሷን አግልላ ቆየች።
ግለሰቧ በረራ ላይ ሳለች ባደረገችው ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባት ስታውቅ ነበር በፈቃዷ ለአምስት ሰዓታት መጸደጃ ቤት ውስጥ ራሷን አግልላ የቆየችው።
ማሪሳ ፎቲዮ የተባለችው መምህርት ከአሜሪካ፣ ቺካጎ ወደ አይስላንድ እየተጓዘች ሳለ ጉሮሮዋን እየከረከራት ነበር።
ቦርሳዋ ውስጥ ይዛው በነበረ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ራሷን ስትፈትሽ ቫይረሱ እንዳለባት አውቃለች።
በረራው እስከሚጠናቀቅ ድረስም መጸዳጃ ቤት ውስጥ ራሷን አግልላለች።
የበረራ አስተናጋጆች ባለችበት ምግብ እና ውሃ አቅርበውላታል።
ከበረራው በፊት የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤቷን ለአየር መንገዱ ስለማቅረቧ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
"አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩትን 150 ሰዎች ቫይረሱን እንዳላስይዛቸው ፈርቼ ነበር" ስትል ለኤንቢሲ ኒውስ ተናግራለች።
መምህርቷ በአውሮፕላኑ መጸዳጃ ቤት ሳለች ቪድዮ ቀርጻ ቲክቶክ ላይ ለቃዋለች። ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ተመልክተውታል።
"በአምስት ሰዓታት ቆይታዬ የምፈልገውን ሁሉ ያቀረበችልኝን የበረራ አስተናጋጅ ላመሰግናት እወዳለሁ። ምግብና ውሃ ከሰጠችኝ በኋላ ደኅንነቴንም ትጠይቀኝ ነበር" ብላለች።
አይስላንድ ስትደርስ ሆቴል ውስጥ ለይቶ ማቆያ ገብታለች።
አሜሪካን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን በፍጥነት እየተሰራጨ ይገኛል።
በአሜሪካ በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በአማካይ 277,000 ደርሰዋል። ይህም ወረርሽኙ ከተነሳ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።
በወረርሽኙ ሳቢያ ሆስፒታል የሚገቡና ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ግን አሁም አነስተኛ ነው።
በኦሚክሮን ምክንያት በርካታ በረራዎች እየተሰረዙ ሲሆን፤ አሜሪካ ውስጥም 1,100 በረራዎች ተሰርዘዋል።