ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ በበዓሉ የተሰረዙ በረራዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ተገለጸ
በአሜሪካ በገና በዓል ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ባገረሸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና በመጥፎ የአየር ጠባይ ምክንያት የተሰረዙ በረራዎች ቁጥር ጣሪያ መንካታቸው ተገልጿል።
በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ በዓለም ዙሪያ ወደ 4 ሺህ 400 የሚጠጉ በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት በአሜሪካ እንደሆነ የአየር ትራፊክ ጣቢያ ድረ-ገፅ ፍላይ አዌር ዘግቧል።
አየር መንገዶች በርካታ ሰራተኞቸቻው የኮሮናቫይረስ በመያዛቸውና ራሳቸውንም አግልለው በለይቶ ማቆያ ላይ በመሆናቸው በዝቅተኛ ሰራተኞች ምክንያት ችግር ውስጥ ገብተዋል።
ይባስ ብሎ የመንገደኞች መስተጓጎል የፈጠረው ደግሞ መካከለኛ አሜሪካ በከባድ በረዶ መመታቷ ጋር ተያይዞ ነው።
በአሜሪካ የበረራ ስረዛዎች መካከል ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑትከቺካጎ ኦሃሬ እና ሚድዌይ አየር ማረፊያዎች ናቸው።
"የዛሬው የበረራ ስረዛዎች ያጋጠመው ሰራተኞች በኦሚክሮን ልውጥ በመያዛቸውና እና ከአየር ሁኔታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ነው። የአየር ሁኔታዎችን በመከታተል በረራዎችን ቀድመን ሰርዘናል። በረራዎቻው የተሰረዙ ተሳፋሪዎችን እንደገና ሌላ በራረ እንዲፈልጉ ወይም ሌላ እቅድ እንዲያወጡ ቀድመን አግኝተን ነግረናቸዋል" ብሏል ዩናይትድ አየር መንገድ በሰጠው መግለጫ።
የዛሬዋ ዕለት እሁድም በርካቶች የገና በዓልን ከቤተሰብ ዘመድ አክብረው ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ሲሆን በረዶ እና ከባድ ንፋስ ያጋጥማል የሚለውን ትንበያ ተከትሎ የበለጠ ተጨማሪ መስተጓጎሎች ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሏል።
"በጣም ረዥም ጊዜ መጠበቅ አለብን፣ የሚበላ ነገር ለማግኘት ቦታ የለም። በጣም ረጅም ጊዜ ነው" ሲል በኦሃራ አየር ማረፊያ በረራው የተሰረዘበት አንድ መንገደኛ በቺካጎ ለሚገኘው ለኤቢሲ ተናግሯል።
ከታህሳስ 15 ጀምሮ በአሜሪካ ከ12 ሺህ በላይ በረራዎች ተሰርዘዋል።
አየር መንገዶች የሰራተኞችን እጥረት ለመቅረፍ ተጨማሪ ክፍያ ሰራተኞችን ለመቅጠር እየሞከሩ ነው። አሜሪካ በኦሚክሮን ልውጥ ምክንያት በኮቪድ-19 ከፍተኛ የቁጥር ማሻቀብ አጋጥሟታል።