በፈረንሳይ በአዲስ ዓመት ዋዜማ 874 መኪናዎች ተቃጠሉ

ፈረንሳይ ውስጥ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በአጠቃላይ 874 መኪናዎች ዶግ አመድ መሆናቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ቢሆንም የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ይህ ቁጥር ከ2019 ጋር ሲነፃፀር የወረደ ነው።

ባለሥልጣናቱ ጨምረው እንደጠቆሙት በዘንድሮው የአዲስ ዓመት በርካታ ሰዎች ለጥቂት ሰዓታት በሕግ ጥላ ሥር እንዲቆዩ ተደርገዋል።

ባለፈው ዓመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል የተጣለውን ሰዓት እላፊ ተከትሎ ፈረንሳይ ምንም ዓይነት ረብሻ አላስተናገደችም።

ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ መኪና ማቃጠል ፈረንሳይ እየተለመደ የመጣ የከተሜዎች ባሕል መሆን ጀምሯል።

በቅርብ ዓመታት ይህንን ድርጊት ለመከላከል ሲባል ቢያንስ 95 ሺህ ፖሊሶች ወደ መንገድ ወጥተው ሲያስሱ ነበር።

የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በየዓመቱ ቢያንስ 32 ሺህ የእሣት አደጋ ሠራተኞች በተጠንቀቅ ቆመው ይጠብቃሉ።

በዋና ከተማዋ ፓሪስ የአፍና አፍንጫ መከላከያ ማድረግ የዜጎችና ጎብኚዎች ግዴታ ነው።

ነገር ግን ይህንን ተላልፈው ተገኝተዋል የተባሉ 779 ሰዎች በከተማዋ ባለሥልጣናት ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

ምንም እንኳ ፈረንሳይ የተወሰኑ የኮቪድ-19 ገደቦችን ብታነሳም ከሰሞኑ በተቀሰቀሰው የኦሚክሮን ዝርያ ምክንያት ሕግጋቱ ተመልሰው ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከሰኞ ጀምሮ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ዝግ በሆነ አዳራሾች መሰባሰብ አይችሉም።

ከዚህም አልፎ ከቤታቸው ሆነው መሥራት የሚችሉ ሰዎች ወደ ቢሮ እንዳይገቡ እግድ ይጣልባቸዋል።

ፈረንሳይ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያዋ ቅዳሜ መቶ ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙባት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።