ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኦስካርን ሽልማት የሚሰጠው አካዳሚ ኃይሌ ገሪማን ከፍተኛ ሽልማት አበረከተላቸው
የኦስካርን ሽልማት በመስጠት የሚታወቀው 'ዘ አካዳሚ ኦፍ ሞሺን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስስ' በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ሙዝየም መክፈቻን አስመልክቶ ከፍተኛ ሽልማቱን ለአንጋፋው ፊልም ሰሪ ኃይሌ ገሪማ አበርክቷል።
በጥቁሮች የሲኒማ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገሪማ 'ዘ አካዳሚ ሙዝየም ኦፍ ሞሺን ፒክቸርስ' የቫንቴጅ ሽልማት የመጀመሪያው ተሸላሚ ሆነዋል።
እንደ 'ሳንኮፋ' እና 'አሽስ ኤንድ ኤምበርስ' ከሚባሉ ምርጥ ፊልሞች በስተጀርባ ያሉት አንጋፋው የፊልም ዳይሬክተር ኃይሌ የሎስ አንጀለሱ ሙዝየም መክፈቻን አስመልክቶ ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ ነው ሸልማቱን የሰጣቸው።
ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገሪማ 'ቫንቴጅ' የተባለውን ሽልማት የተሸለሙበትን ምክንያት አስመልክቶ ሙዝየሙ እንዳስታወቀው "በሲኒማ ዙሪያ ዋነኛ ትርክቶችን በመገዳደርና አውድ በማስያዝ የረዳ አርቲስትና ምሁር" በሚል እንዳከበራቸው አስታውቋል።
ነፃነታቸውን ያላስነኩና ባለራዕዩ ዳይሬክተሩ ኃይሌ ገሪማ ጥናታዊ፣ ታሪካዊና፣ ልብወለድ ፊልሞች ውስጥ በመመላለስ ለአምስት አስርት ዓመታት ያህል ፓን አፍሪካዊነትና የጋራ ትውስታን በፊልማቸው መግለፅ ችለዋልም ሲል ሙዝየሙ በድረ-ገጹ ባሰፈረው ማስታወሻ አሞካሽቷቸዋል።
እንዲሁም ለበርካታ አስርት ዓመታት በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ፕሮፌሰር ሆነው በፊልሙ ዘርፍ ስመ ጥር የተባሉ ሲኒማቶግራፈሮችን ማፍራት ችለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ማሊክ ሰይድ፣ ብራድፎርድ ያንግ እና አርተር ጃፋ ይጠቀሳሉ።
ከሙዝየሙ ድረገፅ በተገኘውም መረጃ መሠረት የኃይሌ ታሪክ ምጥቀትና የሲኒማ ጥልቀት የታየባቸው በርካታ ፊልሞች እንዲሁም እሳቸው ያስተማሯቸውና ተፅእኖ ያሳረፉባቸው ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ።
ሙዝየሙ ለሕዝብ መስከረም 20/2014 ዓ.ም ክፍት የሚደረግ ሲሆን ኃይሌ ከሠሯቸው ፊልሞች መካከልም ምርት ሦስት ሺህ፣ ሳንኮፋ፣ ጤዛ፣ ቡሽ ማማ፣ አሽስ ኤንድ ኤምበርስ፣ አድዋ፣ ዊልሚንግተን 10- ዩኤስኤ 10,000 አና ሌሎቹም ፊልሞቻቸው ይታያሉ።
በዚህ ወር የኃይሌ ገሪማ ሳንኮፋ ፊልም የማርቲን ሉተር ኪንግን ትግል የሚያሳየውን 'ሴልማ'ንና ሌሎች ፊልሞችን በመስራት ታዋቂነት ባተረፈችው የፊልም ባለሙያ ኤቫ ዱቨርኔይ ኩባንያ በአራይ አማካኝነት በኔትፍሊክስ ለዕይታ ይቀርባል።
የባርነትን ትርክት ቀይሯል የሚባልለት የ1993 ሳንኮፋ ጋናን ልትጎበኝ የመጣችና አሰቃቂ የሆነውን በባርነት የተፈነገሉ አፍሪካውያንን ሁኔታ ወደ ኋላ ተጉዛ ካየች በኋላ ከማንነቷ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስለፈጠረች አንዲት ጥቁር ሴት ይተርካል።
ከኃይሌ በተጨማሪ ጣሊያናዊቷን የፊልም ባለሙያ ሶፊያ ሎሬንን ሙዚየሙ 'ቪዥናሪ አዋርድ' የተባለ ሽልማቱን አበርክቶላታል።
ጣሊያናዊቷ ሶፊያ የሁለት ጊዜ የኦስካር ሽልማት አሸናፊ ስትሆን ሙዝየሙም "ሥራዋ የሲኒማ ጥበብን በማላቅ ላደረገችው አስተዋፅኦ" መሸለሙን አስታውቋል።
የአካዳሚው ሙዚየም ዳይሬክተር እና ፕሬዚዳንት ቢል ክሬመር "ለኃይሌ ገሪማም ሆነ ለሶፊያ ሎረን ተፅእኖ ፈጣሪ እና አነቃቂ ሥነ ጥበባት እውቅና መስጠት ክብር ነው" ብለዋል።
ዘ አካዳሚ ሙዝየም ኦፍ ሞሺን ፒክቸርስ በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ የሚገኝ ሲሆን በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ታሪክ፣ ጥበብና ሳይንስ እንዲሁም ባህላዊ ተፅእኖውን የሚያሳይ ነው።
በአሜሪካ ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ትልቅ ሙዚየም ሲሆን በዓለም አቀፋዊ ዕይታ ተዋዝቶ ተወዳዳሪ የሌላቸው ስብስቦችን ያጠናቀረ ሲሆን፤ የሲኒማውን ዓለም ልዩ ምልከታ የሚሰጡ ፕሮግራሞችና ኤግዚቢሽኖችን ያሳያል ተብሏል።
አካዳሚው በፊልሙ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሥነ ጥበቡና የላቀ ደረጃን ላሳዩ ሽልማትም የሚሸልም ሲሆን በስፋት ኦስካር በመባል ይታወቃል።
በጎንደር ከሊቅ ቤተሰብ የተወለዱት ኃይሌ በአሜሪካ ትምህርታቸውን ከመከተታላቸው በፊት በአዲስ አበባ በተዋናይነት ስልጠና ወስደዋል።
በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ መገባደጃ ላይ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ (ዩሲኤልኤ) ኃይሌ ትኩረታቸውን ወደ ፊልም ዳይሬክቲንግ በማዞር ፈር ቀዳጅ የሚባሉ ፊልሞችን ሰርተዋል።
ኃይሌ በዩሲኤልኤ ከአቻዎቻቸው ጥቁር ፊልም ሰሪዎች ቻርለስ በርነትና ጀሊ ዳሽ ጋር በመሆን 'ኤልኤ ሪቤሊየን ግሩፕ' የሚባል መስርተዋል።
ኃይሌ በነጭ የበላይነት የተሞላውን ባህላዊ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ላይ በማመጽና በመገደዳደር የጥቁሩን ማኅበረሰብ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እውነታዎችን በሲኒማው ማሳየት የቻሉ ናቸው ሲሉም በርካቶች ይመሰክሩላቸዋል።
ኃይሌ በሲኒማ ላይ አብዮት ለማምጣት ቁርጠኛ እንደሆኑ ሁሉ ጥቁሮች የሚጨቆኑባቸውና የሚበዘበዙባቸውን ሥርዓቶች ለሚታገሉ የጥቁር ጥበብ ሥራዎችም አክብሮትን ይሰጣሉ።
ከሽልማቱ ጋር በተያያዘ ለዘመናት ሲቃወሙት ከነበረው ሆሊውድ ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንዲሁም በቅርቡ በኔትፍሊክስ በሚቀርበው ሳንኮፋ ፊልም ዙሪያ በኢንተርቴይንመንት ዙሪያ ከሚሰራው ወርሃዊ መጽሔት ከቫኒቲ ፌይር ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
'Haile Gerima on Being Fêted by Hollywood—After Living His Life "in Opposition" to Itበሚል ርዕሱ መፅሄቱ ባወጣው ፅሁፉ ስለ ሽልማቱ እንዴት እንደሰሙ ከቫኒቲ ፌይር ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃይሌ ሲመልሱ፤
"መመላለሶች ነበሩ። በአጠቃላይ በሆሊውድ ላይ ፍላጎት የለኝም። ሆሊውድ የአፍሪካውያንና በአጠቃላይ የጥቁርን ታሪክ የማዛባትና የመበዝበዝ ሁኔታን ስቃወም ነው ህይወቴን ያሳለፍኩት። ብዙ ነገሮች ብዬ አስባለሁ፤ ነገር ግን ዋነኛው ምክንያቱ ኤቫ ናት። እሷ ሥራዬን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስትደግፈው ቆይታለች። ስለዚህ እኔም እሞክራለሁ" በማለት መልሰዋል።
በተለይም ለዘመናት ሆሊውድን ከመቃወማቸውና የአካዳሚው ፖለቲካም ሆነ የምዕራቡ አለም ትርክቶች የማይጥማቸው የፊልም ባለሙያ ከመሆናቸው አንጻር መጽሔቱ የጠየቃቸው አሁን በአካዳሚው መከበራቸው ሁኔታውን የተወሳሰበ ያደርገዋል ወይ? የሚል ነበር።
"ሙዚየሙ አንድ ነገር ይመስለኛል። ለምን የሙዚየሙ አካል ለመሆን እንደተስማማሁ ሙዚየሙ እየወሰደ ካለው አዲስ አሰራር ጋር መያያዙ በጣም አስፈላጊ ምክንያት ነው። ነጭ ያልሆኑ፣ የተገለሉ የፊልም ባለሙያዎች እንዲካተቱና ሥራዎቻቸውን ለመጠበቅ እና ለማጉላት አንድ ትልቅ ሃሳብ አለ።
"ቀሪው ግን ሁሉም የሚያውቀው ነው። ሆሊውድ ከመቶ ዓመታት በላይ ቀደምት አሜሪካውያንና አፍሪካውያንን ሲያገል እንዲሁም የዘረኝነት መሳሪያ ነበር። እኛ የእነሱ አስተሳሰብ እና የዘረኝነት የመጀመሪያ ሰለባዎች ነበርን። የእሱ አካል የመሆን ፍላጎት የለኝም። ሆሊውድን በመቃወም ሕይወቴን ኖሬያለሁ። በእውነቱ እኔ የሆሊውድ ባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም ሰለባ ነኝ።
"በኢትዮጵያ ገና ታዳጊ እያለሁ በሲኒማው ኃይል ተሳብኩኝ፤ ነገር ግን ለአፍሪካውያን ዘረኛ ነበር። በሲኒማው ተፅእኖ ምክንያት ከነጭ የበላይነት ጎን ቆሜያለሁ። አሜሪካ ስመጣም በከፍተኛ ሁኔታ ቅኝ ከተገዙት መካከል ሆኜ ራሴን አገኘሁት።
"አንዴ ወደ ቺካጎ ከደረስኩ በኋላ የአፍሪካ አሜሪካዊ ማኅበረሰብ ራሴን ነፃ እንዳወጣ ረድቶኛል። በእርግጥ እኔ እራሴን ነፃ ለማውጣት በዩሲኤኤልኤ የሰራሁት የመጀመሪያው ፊልም የታርዛን ሞት (ዘ ዴዝ ኦፍ ታርዛን) ይባላል። ያንን ፊልም የሠራሁት በእውነተኛው የነጭ የበላይነት አምሳያ ከታገተ አንጎሌን ነፃ ለማውጣት ነው።
"እኔ ጎንደር ውስጥ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ጣሊያኖች ትተው በሄዱት ቲያትር ቤት ውስጥ ታርዛንን አፍሪካውያንን ሲገድል አይተን ደግፈነው ነበር። በመሰረቱ ለእኔ ከሆሊውድ የነርቭ መጨረሻዎች፣ የስሜት ህዋሴ አካላት እና ከሌሎች ነገሮች እራሴን ነፃ ለማውጣት የዘላለም ትግል ነው" ሲሉ ለመጽሔቱ አብራርተዋል።