ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውሮፓ ውስጥ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ርችቶች ሰው ገደሉ
አውሮፓ ውስጥ አዲሱን የ2022 ዓመተ ምሕረት መግባት ተከትሎ በተተኮሱ ርችቶች ምክንያት ሶስት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል።
ኔዘርላንድስ ውስጥ አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ በርችት ምክንያት ሲሞት አንድ ሌላ ግሰለብ ደግሞ ክፉኛ ቆስሏል።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ታዳጊው የሞተው አንድ አዋቂ ግለሰብ ቤቱ ያዘጋጀውን ርችት ለማፈንዳት ሲሞክር አጠገቡ ቆሞ ሲመለከት በደረሰበት አደጋ ነው።
የኔዘርላንድስ ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አውሎታል።
ጀርመን ውስጥ ደግሞ አንድ የ37 ዓመት ግለሰብ በምዕራባዊቷ ሄኔፍ ከተማ በርችት ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል።
ፖሊስ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ወቅት የተከሰተውን እየመረመርኩ ነው ብሏል።
የጀርመን ዜና ወኪል ዲፒኤ እንደዘገበው ጀርመን ውስጥ ሌሎች በርካታ አደጋዎች በርችት ምክንያት ደርሰዋል።
ዴይሊ ቴሌግራፍ የተሰኘው ጋዜጣ እንደፃፈው ኔዜርላንድስ ውስጥ ቢያንስ 80 ሰዎች በርችት ምክንያት እጅና እግራቸውን እስከማሳጣት የሚያደርስ አደጋ ደርሶባቸዋል።
ኔዘርላንድስም ሆነች ጀመርን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ርችት እንዳይሸጥም ሆነ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከልክለው ነበር።
የደች ባለሥልጣናት ሆስፒታሎች በርችት ምክንያት የሚደርሱ አደጋዎችን ለማከም ጊዜ የላቸውም ብለው ነበር።
ሁለቱም ሃገራት ርችት ጥቅም ላይ እንዳይውል ቢከለክሉም ሕጉን የተላለፉ ሰዎች አደጋ አድርሰዋል።
በርካታ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ርችት ገዝተው የመጡ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ራሳቸው ቤት ውስጥ ሠርተውታል።
ኦስትሪያ ውስጥ እንዲሁ በተመሳሳይ በርካታ ሰዎች አደጋ ሲደርስባቸው አንድ የ23 ዓመት ወጣት ሕይወቱን አጥቷል።