መንግሥት ያጋጠመውን ተጨማሪ ወጪ ለመሸፈን የ122 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ አቀረበ

የገንዘብ ሚኒስቴር በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጥያቄ አቀረበ።

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ገንዘብ በማስፈለጉ እና መንግሥት በሚሰበስበው ገቢ ያለውን የክፍያ ጥያቄ መመለስ አዳጋች በመሆኑ እንዲሁም ያለውን የተጨማሪ ወጪ በበጀት ሽግሽግ መሸፈን ባለመቻሉ ተጨማሪ በጀት ማዘጋጀት አስፈልጓል።

ይህ ተጨማሪ በጀት ለአገር ደኅንነት ማስጠበቂያ፣ ለሰብአዊ እርዳታ፣ በጦርነትና ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ እንዲሁም ለሌሎች አስፈላጊ የመንግሥት ሥራዎች ማስፈጸሚያነት የሚውል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አመልክቷል።

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ አንድ ዓመት በላይ የሆነው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመስፋፋት ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ሲሆን መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ በማስወጣት በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ ይነገራል።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ወጪዎችን ለመሸፈን ባለፈው ዓመትም 26.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መጽደቁ ይታወሳል።

በወቅቱ እንደተገጸው በ2013 ዓ.ም ተጨማሪ በጀት ያስፈለገው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ ላጋጠሙ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች የእለት እርዳታ አቅርቦት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል ነበር።

በዚህ ዓመት በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የቀረበው የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከአራት እጥፍ በላይ ጨምሮ 122 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ይህ የተጨማሪ በጀት ጥያቄው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ለሕህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ ሲሆን፣ ተቀባይነት ካገኘ በቀጥታ ሥራ ላይ እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ2014 ዓ.ም ከፍተኛውን ዓመታዊ በጀትን ማጽደቋ ይታወሳል።

የአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄድ ላይ ሲሆን የዚህ ዓመት በጀት ግን 561 ቢሊዮን ብር ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል።

ይህም በጀት ከ2013 ዓ.ም በ85 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሎ በአገሪቱ መንግሥት የበጀት ታሪክ ከፍተኛው ለመሆን ችሏል። አሁን የተጠየቀው ተጨማሪ በጀት ሲታከልበት ደግሞ አጠቃላይ የዓመቱ በጀት ከ680 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል።