አንዳንድ ነጥቦች አዲስ ስለሚቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ይህንን ሂደት የሚመራና የሚያስተባብር አካል ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

የተለያዩ አላማዎችን አንግበው በፖለቲካው መድረኩ ላይ ያሉ ኃይሎችና ልሂቃን እንዲሁም ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችና ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ እንዲቀራረቡ በማድረግ ለአገራዊ አንድነት ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አገራዊ ምክክሩ አውንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።

የሚቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለአስርታት ምላሽ ሳያገኙ መግባባት ያልተደረሰባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችን በማንሳት ታላላቅና ተከታታይ አገራዊ ምክክሮችን አሳታፊ በሆነ መንገድ በማካሄድ መግባባትን መገንባት ዋነኛ አላማው ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም ያጸደቀው እና ላለፉት ሁለት ወራት ሲረቀቅ ብሎም ውይይቶች ሲደረጉበት የቆየው "የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን" አዋጅ መነጋጋሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

ቢያንስ ሁለት ጊዜ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ያለፈው አዋጁ በርካታ አስተያየቶችና ትችቶችን ሲያስተናግድ ቆይቶ ነው ወደ ሥራ እንዲገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው።

በቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአሁኑ የፍትሕ ሚኒስቴር አርቃቂነት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መሪነት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ስላለው አዲሱ ኮሚሽን አንዳንድ ነጥቦች።

የኮሚሽነሮች ሹመት

በአዋጁ የዜሮ ረቂቅ ላይ ሰባት ኮሚሽነሮች ይሾሙለታል ተብሎ የተጠቀሰ ሲሆን ቀጥሎም ተሻሽሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ላይ የኮሚሽነሮች ቁጥር ወደ 11 ከፍ ተደርጓል።

የመጀመሪያው ረቂቅ ዋና ኮሚሽነር እና ሌሎች ኮሚሽነሮች የሰላም ሚኒስቴር ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ጥቆማ በመቀበል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ ያወሳ ነበር።

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት ዕጩዎቹን ለተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ያሾማሉ ሲል የመጀመሪያው ረቂቅ ያትት ነበር።

ነገር ግን የጸደቀው አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከሕዝብ፣ ከሲቪል ማኅበራት እና ከፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚቀበል እና አፈ ጉባኤው ለምክር ቤቱ ዕጩ ኮሚሽነሮችን እንደሚያቀርብ ያትታል።

"ምክንያቱም የዕጩዎችን ጥቆማ መቀበል እና ለምክር ቤቱ አቅርቦ የማሾም ሥልጣን የአፈ ጉባኤው እና የጽህፈት ቤታቸው ሲሆን ይህ የኮሚሽነሮቹ ገለልተኝነት የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል" ሲል የጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ ይጠቅሳል።

በቅድሚያ በረቂቅ ሕጉ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ሥልጣን ሊሰጥ የነበረው ሐሳብም በመጨረሻ ውድቅ ተደርጎ የአፈ ጉባኤው ሥልጣን አንዲሆን ተደርጓል።

የኮሚሽነሮቹ መብቶች

በአዋጁ አንቀጽ 15 መሰረት በኮሚሽነርነት የሚሾሙት አባላት ያለመከሰስ መብት አግኝተዋል። እንዲሁም "የኮሚሽነሮች ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ለመንግሥት ከፍተኛ ተሿሚዎች በተፈቀደው ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም አግባብ ይፈፀማል" ሲል አዋጁ ያስቀምጣል።

በኮሚሽኑ ሥራ ላይ ድምጽ የመስጠት ብሎም ለሥራቸው የሚያስፈልጉ ሰነዶቸን እና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን የማግኘት እና የመመልከት መብት አላቸው። ይህንንም በሥራ ላይ ያገኙትን ምስጢር የመጠበቅ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ስለ ኮሚሽኑ ሥራዎች

ኮሚሽኑ በጀቱ በመንግሥት የሚመደብ ሲሆን የመንግሥትን የፋይናንስ አስተዳደር መርሆዎችን መሰረት በማድረግ በበጀቱ ላይ ሙሉ ነጻነት እንደሚኖረው አዋጁ ያደርጋል። ኮሚሽነሮቹ አባል የሆኑበት ምክር ቤት ዋናውን የኮሚሽኑን ሥራዎች የሚያከናውን ይሆናል።

ምክር ቤቱ ለምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን መምረጥ፣ ከኮሚቴዎችም ሆነ ከሕዝብ የሚገኙ ምክረ ሐሳቦችን ለመንግሥት ማቅረብ፣ ለኮሚሽኑ እንቅስቃሴ የሚያስፈለጉ የውስጥ ደንብ እና መመሪያዎችን ማውጣትን ጨምሮ መሠረታዊ የአስተዳዳራዊ ተግባራትን ጨምሮ በበላይነት ይመራል።

በሕብረተሰቦች መካከል የሚታዩ መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያቶችን በመለየት እና ለውይይትም ርዕሰ ጉዳዮችን በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው የሚለየው ይሔው ኮሚሽን ነው።

እንዲሁም እነዚህ ምክክሮች "ብቃት ባለው ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፤ ያለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስስ አጀንዳ ላይ የሚያተኩ፣ ግልጽ ብሎም ለማስፈጸም የሚያስችሉ ውጤታማ አገራዊ ውይይትን የሚያስተናግድ ሥርዓትን የመዘርጋት" ሥልጣንም ተሰጥቶታል።

የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ

በአዋጁ ዜሮ ረቂቅ ላይ ለሁለት ዓመት የሚቆይ እድሜ ይኖረዋል የተባለው ኮሚሽኑ በአንድ ዓመት ከፍ ብሎ የሦስት ዓመት የቆይታ ዘመን እንዲኖረውም ተደርጓል።

ነገር ግን እንዳስፈላጊነቱ በተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜው ሊራዘም እንደሚችል እና እድሜው መሰላት የሚጀምረው ኮሚሽነሮቹ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ መሆኑም በአዋጁ ተካቷል።

ዋና መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ሆኖ እንዳስፈላጊነቱ በክልሎች ቅርንጫፎች ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል።

የኮሚሽኑ ሥልጣን

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ አላማ መንግሥታዊ በሆኑም ሆነ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ የምክክር ሂደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን በማጥናት በቀጣይ ለሚያካሂዳቸው አገራዊ ውይይቶች በግብአትነት እንደሚጠቀም አዋጁ ያስረዳል።

በልሂቃኖች መካከል አገራዊ ጉዳዮችን አስመልከቶ ያሉ ልዩነቶችን የመለየት፣ ምክክሮችን የማሳለጥ እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚወከሉ ተሳታፊዎች ያሉባቸውን የምክክር ስብሰባዎችን ያካሂዳል።

ኮሚሸኑ ተወካዮችን የመምረጥ ብሎም ኮሚሽነሮቹ እነዚህን ምክክሮችን የመምራት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

እንዲሁም የምክክር አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን ተግባር ላይ ሊውሉ ስለሚችሉበት መንገድ ሪፖርቶችን በማሰናዳት ለመንግሥት እና ለሕዝብ የማቅረብ ግዴታም ተጥሎበታል።

መንግሥት ምክረ ሐሳቦችን እንዲተገብር የማገዝ ብሎም ተግባራዊነታቸውን የመከታተል ሥልጣንም አግኝቷል።